በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ መገንባት ለብሄራዊ መግባባት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ገለፀ።

በዞኑ የመረጃ ተደራሽነት በማሳደግ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ማህበረሰቡ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል ።

መምሪያው በ2014 በጀት አመት የመጀመሪያ ግማሽ አመት አፈፃፀም ግምገማና የቀጣይ እቅድ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ግምገማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በግምገማ መድረኩ እንደገለፁት የተቋሙ ዋና ተልዕኮ በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብ በመገንባት በሂደት በመረጃ የተመሰረተ ውሳኔ የሚሰጥና በተጨማሪም ለብሄራዊ መግባባት የራሱ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ህዝብ መፍጠር እደሆነ ገልፀዋል።

ይህ ግብ ለማሳካት በዞኑ የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የመረጃ ተደራሽነት ለማሳደግ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል።

በዞኑ የሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን የገለፁት አቶ መብራቴ እነዚህ እንቅስቃሴዎች የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም መረጃ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይ ዞኑ የራሱ የሚዲያ አማራጮች ለማስፋት እየሰራ
ቢሆንም እስከዚያው ከሌሎች የሚዲያ ተቋማት ጋር በቅንጅት የመስራቱ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ኃላፊው ገልጸዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ በየደረጃው የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመሰብሰብና በማደራጀት ለመንግስት ተደራሽ ከማድረግ አንፃር የተጀመሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው በቀጣይ መምሪያው መሰል ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልፀዋል።

የማህበረሰቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት በየደረጃው ተቋሙ በተገቢው የሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ ከማደራጀት አንፃር ውስንነቶች መኖራቸው ጠቁመው በቀጣይ ለመረጃ ቅርብ የሆነና በመረጃ የተመሰረተ ውሳኔ የሚሰጥ ህብረተሰብ ለመፍጠር በየደረጃው የሚመለከታቸው አካላት ተቋሙ በቅርብ መከታተልና መደገፍ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል ።

በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቬዥን ድርጅት የወልቂጤ ኤፍ ኤም ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ወልዴ በበኩላቸው የኮሚኒኬሽን መምሪያ ሚዲያዎችን በማስተባበር በዞኑ የሚከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልፀው በቀጣይ ከዚህ የበለጠ በቅንጅት መስራት አለበት ብለዋል።

ለዚህም ተቋማቸው የሚጠበቅበትን ሁሉ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም ገልፀዋል።

ወልቂጤ ኤፍ ኤም የዞኑ ህብረተሰብ የመረጃ ፍላጎትን ለማርካት የስርጭት አድማሱን የማስፍት ስራ በዞኑ ምስራቅ ወረዳዎች አካባቢ መስራቱ ገልፀው ከጥራት አንፃር የሚነሱ ችግሮች ለመፍታት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

አቶ ዳርሞሎ ከድር ከቡታጅራ ከተማና አቶ ደጋጋ እንዳሻው ከማረቆ ወረዳ የመድረኩ ተሳታፊዎች ሲሆኑ በጋራ በሰጡት አስተያየት የተካሄደው የግምገማ መድረክ የተሰሩ መልካም ስራዎችን አጠናክረው ለማስቀጠልና ያልተከናወኑ ተግባራት በቀጣይ ለማከናወን ግብአት እንዳገኙበትም ገልፀዋል።

አክለውም በዜጎች ቻርተር ውይይት አስፈላጊነትና ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት ላይ የተፈጠረላቸው ግንዛቤ አዲስ ወደ ተቋሙ የተቀላቀሉ አመራሮች እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ተናግረዋል።

የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም በወረዳና ከተሞች እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የበጀት፣የሰው ሀይልና ግብአት ማነቆ እየሆነባቸው እንደሆነ ገልፀው በቀጣይ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊያግዙ እንደሚገባም ጠይቀዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች አክለውም በየቦታው በፌክ አካውንት የሚያተራምሱ ህገወጦች ከሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ተጠያቂነት የመፍጠርና ዞኑ የራሱ የማህበረሰብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ገንብቶ መውጣት አለበት ሲሉም ገልፀዋል።

በመድረኩም የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊና ባለሙያዎች፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች፣የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።

=ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡

Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *