የበጋ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ስኬታማ ለማድረግና በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት እንዲመጣ ቅንጅታዊ አሰራሩ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያዉ የበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን የእስካሁን አፈጻጸም የቴክኒክ ኮሚቴዉ አባላቶች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።

ወጣቶች በዞኑ የልማት እንቅስቃሴና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በንቅናቄ በመሳተፍ እንደ ሀገር ሆነ አንደ ዜጋ ተጠቃሚ ከሚሆኑባቸው መስኮች አንዱ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ዋነኛውና አንዱ ነው፡፡

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አወል ጅማቶ በግምገማ መድረኩም ተገኝተዉ እንዳሉት በበጋ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወኑ ይገኛል።

በማህበራዊ ቀዉስ ዉስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ችግሮቻቸዉን እንዲቀረፉ በማድረግ ረገድ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተጠናክረዉ መቀጠል አለባቸዉ ብለዋል።

ዋና ዋና ግቦች ላይ ትኩረት በማድረግና ቅንጅታዊ ስራዉ ከመቼዉም ጊዜ በላይ አጠናክሮ በማስቀጠል በበጋዉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የተያዙ እቅዶችን ማሳካት እንደሚገባም አብራርተዋል።

ለዚህም ስኬት የቴክኒክና የአብይ ኮሚቴዎች እያደረጉት ያለዉን ጥረት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ዘርፍ ሀላፊ ቶ አብዱ ድንቁ እንዳሉት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶች ለማህበረሰቡ ልማት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ዕምቅ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን ክህሎታቸውንና ልምዳቸውን የሚያበረክቱበት ትልቅ ተግባር ነዉ።

የበጋ በጎ ፍቃድ ወጣቶች በትምህርት፣ በጤና፣ በማህበረሰብ ልማት፣ በአከባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በትራፊክ ደህንነት በመልካም አስተዳደር በግብርና ልማት ፣ በጽዳትና ዉበት ፣የአረጋዉያንና ለአካል ጉዳተኞች አዲስ ቤት በመስራትና ጥገና በማድረግ ፣ተማሪዎችን በቁሳቁስ በመደገፍና በሌሎችም ተግባራቶች ላይ ወጣቶች ማህበረሰቡን የሚጥቅሙ ስራዎች እየሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል።

በዞኑ በበጋዉ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 4 መቶ 78 ሺህ 11 የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን 2 መቶ 78 ሺህ 4 መቶ 25 ህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አስታዉቀዋል።

በ13 የተለያዩ ተግባራት 182 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ለማሳተፍ እቅድ ተይዞ በዚህም 112 ሺህ 5መቶ 17 ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሆነም አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የሪዕዮተ አለምና ፖለቲካ ዘርፍ ምክትል ሀላፊና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሀዲሙ ሀሰን በበኩላቸዉ በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች በበጋ በጎ ፍቃድ ወጣቶች አበረታች ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለዘርፉ ስኬት የቴክኒክና አብይ ኮሚቴዎች የድጋፍና ክትትል ስራዉ የበለጠ በማጠናከር የሚፈለገዉ ወጤት ማምጣት ይገባል ብለዋል ሲል የዘገዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *