ጉራጌ ዞን በርካታ የቱሪዝም መገኛ ስትሆን ከነዚህም መካከል የተፈጥሮ መስህቦች ባለቤት ናት።

የተፈጥሮ መስህቦች ወይም ሀብቶች የአየር ንብረት ሚዛን ፣ብዝሃ ህይወትና ስነምህዳርን ከመጠበቅ አንፃር ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን እሙን ነው፡፡ የተፈጥሮ መስህቦች ስንል በተፈጥሮ የተገኙ ሐይቆች፣ ወንዞች፣ ተራሮች፣ የተፈጥሮ ደኖች፣ ፍል ውኃዎች፣ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎች፣ የማህበረሰቡ መኖሪያ ቦታዎችና አጠቃላይ ገፅታዎች ያጠቃልላል።

በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየለሙና እየተጠበቁ ያሉትና በሀገር በቀል ዛፎች የተሞሉት በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ጥብቅ ደኖች ለአካባበው ግርማሞገስ ከማላበሳቸውም በላይ የተለያዩ የዱር እንሰሳት አቅፈው ለዞኑ እምቅ የቱሪዝም መስህብ ስፍራ ናቸው፡፡

እነዚህ ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች በመጠቀም ኢኮ-ቱሪዝምን ማስፋፋት ይቻላል፡፡ በኢኮ-ቱሪዝም የአካባቢውን ህብረተሰብ የቤት አሰራርና አኗኗር ባህልን የተከተለ፣ የአካካባቢ ቁሳቁሶችን በግብዓትነት የሚጠቀም የመዝናኛ ማዕከላትን ደኖቹ በሚገኙበት አካባቢ መስራት ያስችላል፡፡

በዞኑ የሚገኙት ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች አብዛኞቹ የዞኑ ህዝብ በብዛትና በጥግግት በሚኖርበት አካባቢ ውስጥ አነስተኛ መጠን ባላቸው ሜዳማ፣ ተዳፋት፣ እና ተራራማ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ፡፡ በዞኑ በየወረዳዎቹ የሚገኙት ጥብቅ የተፈጥሮ ደኖች ወገፐቻ የተፈጥሮ ደን በጉመርና ቸሃ ወረዳ፣ ቆጠር ገድራ በእዣ ወረዳ፣ አፍጥር እና አውሪያ የተፈጥሮ ደን ቸሃ ወረዳ ፣ አምባ እና ቦዥባር በእዣ ወረዳ፣ ቤደር የተፈጥሮ ደን በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳና አሩሲ የተፈጥሮ ደን በሶዶ ወረዳ የሚጠቀሱ ሲሆን ከነዚህም መካከል የቆጠር ገድራ ደን በወፍ በረር ልናስቃኛችሁ ወደድን።

*.የቆጠር ገድራ ደን በወፍ በረር!!

የቆጠር ገድራ ደን በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ልዩ ስሙ ቆጠር ገድራ ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ቀበሌው ከዞን ዋና ከተማ ወልቂጤ 52 ኪ/ሜ ከወረዳው ዋና ከተማ አገና በስተምስራቅ አቅጣጫ 10 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡የቆጠር ገድራ ቀበሌም ሆነ የደኑ ስያሜ ያገኘው በአከባቢው ታዋቂ ከሆነው የቆጠር ጎሳና በወቅቱ አከባቢውን ሸፍኖ ከነበረው ገድራ /አስታ/ ቁጥቋጦ ነው፡፡ ቆጠር የጎሳው ስም ሲሆን ገድራ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ጠፍቷል በሚባል ደረጃ ላይ ያለና በድሮ ዘመን በተለይ በማይታረስ መሬት ላይ በስፋት ይገኝ የነበረው የአስታ /ቁጥቋጦ/ የጉራጊኛ ስም ነው፡፡

የቆጠር ገድራ ደን መነሻ የሆነው የአስታ ቁጥቋጦ ሲሆን የደኑ ክልል ከጥንት ጀምሮ በጎሳው ተከብሮ ይጠበቅ ስለነበረ ከአስታው በተጨማሪ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎች በወፍ ዘራሽነት እየበቀሉና እየተስፋፉ ሲሆን ነባሩ አስታ ደግሞ ለእነዚህ ትላልቅ ዛፎች ቦታ እየለቀቀና እየጠፋ ደኑ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በሀበሻ ጽድ እየተሸፈነ ሊመጣ ችሏል፡፡ የሀበሻ ጽድ በጣም ጠንካራና በቀላሉ በአፈርም ሆነ በምስጥ የማይበላና ሳይበሰብስ ለረጅም ዘመናት ሊቆይ የሚችል በመሆኑ የጉራጌን ብሔረሰብ ከሌሎች ብሔረሰቦች የሚለየውን ውብ ባህላዊ ቤት ለመገንባት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

የጉራጌ ባህላዊ ቤት ከአጠና፤ ከቀርክሃ፤ ከገመድና ከክዳን ሳር ውጪ የውጪም ሆነ የውስጥ ግንባታው ሁሉ (ግድግዳው፤ ምሰሶውና ጣውላው) የሚሰራው ከዚሁ ከሀበሻ ጽድ አለያም ከባሀርዛፍ ነው፡፡

የቆጠር ገድራ ደን በአጠቃላይ የቆጠር ጎሳ የጋራ ሀብት ሲሆን ለአከባቢ ልማትና ለአከባቢያዊ ችግሮች በማቃለል በኩል ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል፡፡ የቀበሌው አጠቃላይ መሰረተ-ልማቶች የሚሰሩት በዚህ ደን ሲሆን የቆጠር ገድራ ት/ቤት ከ1ኛ ደረጃ እስከ መሰናዶ በማድረስ፤ የጤና ጣቢያ አገልግሎት፤ የንጹህ ውኃ አገልግሎትና ደኑን አቋርጦ ከአገና ወደ ሻመነ የሚደርሰው መንገድን የመሳሰሉ የቀበሌ ልማቶች ሲሰሩ በአከባቢ ህዝብ ለሚደረገው ተሳትፎ መላው የጎሳው አባላት ተወያይተው ከደኑ የተወሰነ በመሸጥ ለዚህ ልማት እንዲውል የሚደረግ ሲሆን የዚህ ዓይነት ሽያጭ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡

የቆጠር ገድራ ደን ባሁኑ ወቅት ጠቅላላ ስፋቱ እን0 ሄ/ር ሲሆን ከማንኛውም ዓይነት ንክኪ ውጭ ሆኖ ህብረተሰቡም የደኑን የልማት ባለውለታነት በመገንዘብ ልክ እንደ ዓይኑ ብሌን ጥበቃና እንክብካቤ ያደርግለታል፡፡

ከዚህ ደን ዛፍ መቁረጥ ቀርቶ የወደቀው ዛፍ እንኳ ያለ ጎሳው እውቅና እንዳይነሳ ቃለ መሃላ በመግባት ከውስጥም ሆነ ከውጪ ደን ጨፍጫፊዎች እየተከላከለው ይገኛል፡፡ በዚህ ደን ውስጥ ከሀበሻ ጸድ በተጨማሪ አልፎ አልፎ የኮሶና የዝግባ ዛፎች ይገኛሉ፡፡የቆጠር ገድራ ደን ችግኝ ጥቅጥቅ ብሎ ከሩቅ ለሚመለከተው በባለሙያ የተከረከመ እሰከሚመስል ድረስ ተፈጥሮ ራሱ ከርክሞ ለአከባቢው ልዩ ውበትና ግርማ ሞገስ አላብሶት ይገኛል፡፡

የቆጠር ገድራ ደን በ2003 ዓ.ም ደንነቱ ብቻ ሳይሆን ሌላም ትልቅ ቁም ነገር (መስህብ) አምቆ እንደያዘ ይፋ ሆነ፡፡ ይኸውም በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደነበሩ የተነገረላቸውና በውስጣቸው በርካታ ኃይማኖታዊ ቅርሶችን የያዙ 10 የተለያዩ ዋሻዎች መገኘታቸው ነው። ዋሻዎቹን በሚመለከት ዝርዝር መረጃ በሌላ ጽሁፍ እራሱን አስችሎ የሚቀርብ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከአስሩ ዋሻዎች ሦስት ዋሻዎች አገልግሎት እየሰጡና ለጎብኚዎች ክፍት ሆነው ይገኛሉ፡፡

ውድ አንባቢያን እንግዲህ ስለቆጠር ገድራ ደን ስናወሳ እነዚህን ዋሻዎችንም ታሳቢ በማድረግ ስለሆነ ደኑን ለመጎብኘት ሲመጡ በእግረ መንገድ የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ፣ ቲናው አበባ አ/ማ፣ ኤደን ውኃ አ/ማ፣ አገና ከተማ መገቢያ ላይ የሚገኘው እጅግ ዘመናዊ የሆነው ደሳለኝ ሎጅ እንዲሁም የእዣ ወረዳ ተፈጥሮአዊ መልክዓ-ምድርን እየጎበኙና እያደነቁ ስለሚሆን ይህን ውብ ስፍራ እንዲጎበኙት የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ይጋብዞታል፡፡

መስህቦቻችን በተገቢ ለይተን እንጠብቅ፣ እንከባከብ፣እናስተዋውቅ፣እንጎብኝ መልክታችን ነው።

የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *