በሀገሪቱ የሚቃጡ ጥቃቶች በመመከት ህልውናዋን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸው በጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ ህዝባዊ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።

በሶዶ ወረዳ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ 571 ህዝባዊ የሰራዊት አባላት ዛሬ ተመረቁ።

ከተመራቂዎቹ መካከል ገግሬ ረታ እና ማረኝ ጫካ የህዝባዊ ሰራዊት ምሩቃን ተጠቃሾ ናቸው።

እንደ ተመራቂዎቹ ገለጻ አሸባሪው የህወኀት ቡድንና ተላላኪዎችን በሀገሪቱ የፈጸመው ክህደትና አስነዋሪ ድርጊት በመመከት ህልውናዋን ለማስከበር አስፈላጊውን መስዋዕት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ተናግዋል።

ሀገሪቱ ለማሸበር በየቦታው የተሰማሩ የቡድኑ ደጋፊዎች የጥፋት ተልዕኮአቸው ለማምከን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

ደረጄ ባሩዳ እና ድንቁ ሻንቆ በበኩላቸው ስልጠናው ብቁና አካባቢያቸው በንቃት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም በስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ በመጠቀም በአካባቢያቸው ያልተለመደ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግለሰቦች ከመከታተል በተጨማሪ የለውጡ ደጋፊ መስለው አላስፈላጊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት ተከታትለው በመያዝ እንደሚያጋልጡ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ተገኝተው እንደተናገሩት የቀደሙ አባቶች በአንድነት ነጻነቷን አስከብረው ያቆዩዋት ሀገር ለተተኪው ትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

አሸባሪው የህወኀት ቡድን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር በሀገሪቱ የከፈተው ጦርነት ከባድ ቢሆንም በህዝቡ የተባበረ ክንድ መመከት እንደተቻለ አስረድተዋል።

ቡድኑ ሀገር የማፍረስ ሴራው ከሽፎ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት በመሆኑ እጅ የመስጠት ብቸኛ አማራጩ መጠቀም አለበት ብለዋል።

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች ህዝባዊ ሰራዊት በማደራጀትና ህብረተሰቡ አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸው የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው በህዝባዊ ሰራዊት የተመረቁ ሰልጣኞች የአካባቢያቸው ሰላም ለማረጋገጥ ተግተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኦንጋዮ ኦዳ በአባቶች መስዋዕትነት የተረክብናት ነጻ ሀገር ነጻነቷን አስከብረን ለትውልድ የማስተላለፍ ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ብለዋል።

ምልምል ህዝባዊ የሰራዊት አባላት ከአካባቢያቸው ባለፈ ለሀገሪቱ ደጀን በመሆናቸው አደረጃጀቶቻቸው አጠናክረው በልማት ስራው ጭምር በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ተካ የወረዳው ነዋሪዎች የአካባቢው ብሎም የሀገሪቱ ሰላም በማረጋገጥ ሂደት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ተመራቂዎች የአካባቢያቸው ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ድንገተኛ ፍተሻ በሚደረግበት ወቅት ድንገተኛ ፍተሻ የሚያካሄዱ ሲሆን የተለየ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አካላት በመከታተል ማንነታቸው ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የሶዶ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሴ አበጋዝ የወረዳው ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በሁሉም ቀበሌዎች ህዝባዊ አደረጃጀት ለመፍጠር 571 ሰልጣኞችን በመሰረታዊ ወታደራዊ ስልጠና በማሰልጠን ማስመረቅ እንደተቻለ ገልጸዋል።

ምሩቃን የተጣለባቸው ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ አስተዳዳሪው መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

  • አካባቢህን ጠብቅ!
  • ወደ ግንባር ዝመት!
  • መከላከያን ደግፍ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *