ከፌዴራል ፣ከክልል እና ከዞን የተዉጣጡ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳና በወልቂጤ ከተማ በሴቶች የልማት ህብረት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተዛዙረዉ ጎብኝተዋል።
በቸሃ ወረዳ አዘር ቀበሌ ቆሮሚያ የሴቶች የልማት ህብረትና በወልቂጤ ከተማ እድገት ጮራ ቀበሌ ኒመኒ የሴቶች የልማት ህብረት እንዲሁም በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ዋንስቶፕ ማዕከል ሸመነ ክሊኒክ ተዛዙረዉ ጎብኝተዋል።
በመስክ ምልከታዉ ላይ የተገኙት የፌዴራል ሴቶችና ማህበራዊ ሚኒስቴር የህጻናት መብት ስርጸትና ስብዕና ቀረጻ ዴስክ ሀላፊ አቶ በለጠ ዳኜ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሴቶችና ህጻናትና የሚሰሩ ስራዎች ክትትል የማድረግ ስራ በሁሉም ክልሎች እየተካሄደ ነዉ ብለዋል።
እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን ጥሩ አፈጻጸም መኖሩም አመላክተዉ በዚህም በዛሬዉ ዕለት በቸሃ ወረዳ በሴቶች የልማት ህብረት እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የሴቶች የልማት ህብረት እንቅስቃሴ ተዛዙረዉ የተመለከቱ እንደሆነና በዚህም ሴቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ዉጤታማ ስራ እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
የፌዴራል መንግስት የተለያዩ ፖሊሲዎች የሚያወጣ እንደሆነም ጠቁመዉ ሴቶች በኢኮኖሚያዊ ፣በማህበራዊና በፖለቲካዊ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸዉ ለማረጋገጥ በመስክ ምልከታ ተች ድረስ በመዉረድ እያዩም እንደሆነም አብራርተዋል።
ሴቶችን በዋናነት ተጠቃሚ ለማድረግ ሴቶች በልማት ህብረት አደረጃጀት መታቀፍ እንዳለባቸዉና እነዚህ አደረጃጀቶች ምን ያህል ዉጤታማ እንደሆኑና እየሰሩ እንደሆነም በመስክ ምልከታ የሚያረጋግጡ እንደሆነም አመላክተዋል።
በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ አዘር ቀበሌ 6 ሄክታር መሬት ጤፍ አልምተዉ ስራ እየሰሩ ያሉና በቤተሰብ ደረጃ ሴቶች የጓሮ አትክልት በማልማት እንዴት ተጠቃሚ እንደሆኑና በተለይ በትምህርት ፣በጤና ፣በግብርና ከፍትህ ጋር ከቀበሌ እስከ ዞን ያሉ ቅንጅታዊ አሰራሩ የሚበረታታ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ጥሩ ስራ እየሰሩ ያሉ ሴቶች ተሞክሮቻቸዉን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዉ እነዚህም ሴቶች የተለያዩ ማበረታቻ በመስጠት የበለጠ ዉጤታማ ስራ እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚገባም አስታዉቀዋል።
ለችግር የተጋለጡ ህጻናቶች በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲደገፉ ማድረግ እንደሚገባና ህጻናት መደመጥንና ሀሳባቸዉ በነጻነት ማካፈል እንዲችሉ በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተናግረዋል።
የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ነጅብያ መሀመድ እንዳሉት ከ2016 ዓመተ ምህረት ጀምሮ በዋናነት የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀት ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ ዉጤታማ ስራ እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
ሴቶች በግልና በቡድን በመሆን የቁጠባ ባህላቸዉ እያደገ እንደሆነም አመላክተዉ በዞኑ በሴቶችና በህጻናትም ዘርፎች ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አብራርተዉ ሴቶች በሰበል ብዜት በድለባና በእርባታዉ በገንዘብ ቁጠባና ጉልበት በሚቆጥቡ ተስማሚ ቴክኖሎጂዎች በዕደ ጥበብ ስራዎች ላይ የማተኮር ስራዎች ላይ እየሰሩም እንደሆነም ጠቁመዋል።
ዛሬ በቸሃ ወረዳ አዘር ቀበሌ ቆሮሚያ የሴቶች የልማት ህብረት ተዛዙረዉ የጎበኙ እንደሆነና የልማት ህብረቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸዉ ለማረጋገጥ 6 ሄክታር መሬት በጤፍ መሸፈን የቻሉና በግልና በቡድን በመሆን የሚቆጥቡ ሲሆን በቡድን ከ350 ሺህ ብር በላይ የቆጠቡ እንደሆነና ከዚህም በተጨማሪ በቤታቸዉ ዶሮ በማርባትና ዉጤታማ የጓሮ አትክልት ስራ እየሰሩም እንደሆነም አስረድተዋል።
በትምህርት በጤናና በማህበራዊ እንዲሁም ከወቅታዊ የወባ በሽታ በመከላከል ዘርፎች ሴቶች ሞዴል ስራ እየሰሩም እንደሆነም አስረድተዉ ህጻናት በመደገፍ ረገድም አበረታች ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ እስከ 53 ሄክታር መሬት እያለሙ ያሉ የሴቶች የልማት ህብረት መኖራቸዉ ያመላከቱት ሀላፊዋ ይህንን አስፍቶ ከመሄድ ጋር በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ሸመነ ክልኒክ ዋን ስቶፕ ሴንተር አንዱ የተጎበኘ እንደሆነም ተናግረዉ ይህም የህጻናቱ ችግር ለመፍታት እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሌላኛዉ በጉብኝቱ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ቢሮ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ባለሙያ አቶ አዲስ አኖሎ እንዳሉት በቸሃ ወረዳ በቆረሚያ የሴቶች የልማት ህብረት እየተሰሩት ያለዉ ዉጤታማ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነዉ ብለዋል።
በቸሃ ወረዳ አዘር ቀበሌ የቆረሚያ የሴቶች የልማት ህብረት ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ ኮሬ እንዳሉት ህብረታቸዉ 30 አባላት ያሉትና አሁን ላይ 6 ሄክታር መሬት በጤፍ ማሳ የሸፈኑና ከ350 ሺህ ብር በላይ ቁጠባ እንዳላቸዉና ከዚህም በተጨማሪ በግል እንደሚቆጥቡና እንዲሁም በጓሮ አትክልትና በዶሮ እርባታ ዉጤታማ ስራ እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
በወልቂጤ ከተማ እድገት ጮራ ቀበሌ ኒመኒ የሴቶች የልማት ህብረት ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲሃ አብድልፈታ በበኩሏ 24 አባላት ያላቸዉና ከ170 ሺህ ብር በላይ የመቆጠብ እንደቻሉና የልማት ህብረት በመጋዘን እህል ገዝተዉ በማስቀመጥና በመሸጥ ዉጤታማ ስራ እየሰሩ መሆነም ተናገረዋል።
በመጨረሻም ከሚንስቴር መስሪያ ቤት እና ክልል ቢሮ የመጡ አካላት ከቀበሌ ልማት ህብረት ጀምሮ የታዩ ተግባራት እንዲሁም እንደ ዞን የተሰሩ ስራዎች አፈፃፀም መነሻ በማድረግ ለዞኑ የማኔጅመንት አካላት ግብረመልስ የሰጡ ሲሆን ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ይበልጥ ሴቶችና ህፃናት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።