ጥቅምት 23/ 2017 ዓ.ም
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ በኩታ ገጠም የለማው የጤፍ ማሳ አበረታች መሆኑን የጉራጌ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የፌደራል፣ የክልልና የዞኑ ግብርና መምሪያና ባለድርሻ አካላት በእኖር ወረዳ ዳአምር ቀበሌ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል በኩታ ገጠም በ25 ሄክታር መሬት የለማው የጤፍ ማሳ የመስክ ምልከታ አደረጉ።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት መንግስት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መርህ የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት መምሪያው በ2016/17 በጀት አመት በመኸር እርሻ ልማት 4መቶ 92 ሄክታር መሬት በጤፍ፣በገብስና በስንዴ ለማልማት ታቅዶ 3መቶ 56 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏል።

ከለማው ጠቅላላ ማሳ ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ኃላፊው አመላክተዋል።

ኃላፊው አክለውም ይህንንም እቅድ ለማሳካት ከዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እቅዱ የጋራ በማድረግ እያንዳንዱ ምዕራፍ የድርጊት መርሀ-ግብር ተቀምጦለት ወደ ትግበራ መግባት መቻሉንም ገልጸዋል።

በጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጊዜ ወርቅ አለሙ በበኩላቸው ከዞን እስከ ቀበሌ የተለያዩ የአመራርና የህዝብ ውይይት መድረኮች በዞኑ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እየተመራ ውይይቶች በማካሄድና በመግባባት ሁሉም ወረዳ ያለው እምቅ አቅም በመለየት እንዲያለሙ መደረጉን ገልጸው በዚህም አበረታች ስራ መስራት መቻሉን ተናግረዋል።

ኃላፊዋ አክለው እንደገለፁት በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች፤ የድሀ ድሀ የሆኑ ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች፤ የምግብ እጥረት የገጠማቸው አጥቢ እናቶችና ከ5 አመት በታች እድሜ ላይ ያሉ ህፃናት መረጃ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት መረጃ የማጥራት ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በተለየው መረጃ መሰረት ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎችን በራስ አቅም ድጋፍ እንዲደረግ ለማስቻል ሁሉም ወረዳ ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም 3 መቶ 56 ሄክታር መሬት በማረስ በጤፍ፤ በስንዴና በገብስ መሸፈን ተችሏል ነው ያሉት።

የሰብአዊ ድጋፍ በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት ከፈፀሙ ወረዳዎች አንዱ እኖር ወረዳ ሲሆን 45 ሄክታር መሬት በጤፍ መሸፈን መቻሉን የገለጹት ኃላፊዋ ከዚህም 25 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ማልማት እንደተቻለ ተናግረዋል።

የለማው ማሳ የፌደራል፤የክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር እና የዞንና የወረዳው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በወረዳው ዳአምር ቀበሌ በመገኘት የመስክ ምልከታ መደረጉንም አንስተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *