የጉራጌ የመስቀል በዓል የአከባበር ስርዓት የአደባባይ በዓል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

7ኛው ዙር መስቀል በጉራጌ ልዩ ፌስቲቫል በዞኑ በእኖር ወረዳ በገሀራድ ቀበሌ ቱባ ባህላዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ።

የመስቀል በዓል የጉራጌ ማህበረሰብ ትውፊቱን የሚያሳይበትና ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያከናውንበት በመሆኑ ይበልጥ ማስተዋወቅ እና ማበልጸግ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ኑሪ ከድር እንደገለጹት መስቀል በጉራጌ በርካታ የሀገርና የውጭ ቱሪስቶች አይን ማረፊያ በመሆኑ በዓሉ ለመታደም በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ስራ ወዳዱና የታታሪዎቹ መንደር ወደ ጉራጌ ቀዬ የሚተሙበት በዓል ሆኗል ብለዋል።

በዓሉ የተቸገሩ የሚረዱበት የተጣሉ የሚታረቁበት በተጨማሪም ሙዚቃ፣ ቲአትር እና ስነ ጹሁፉም ጎልቶ የሚንጸባረቅበት እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የሚፈጥር ታላቅ በዓል እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ የመስቀል በዓል የአከባበር ስርዓት የአደባባይ በዓል ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራበት የቢሮ ምክትል ኃላፊው አቶ ኑሪ አስታውቀዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት የመስቀል በዓል ከመንፈሳዊ እና ከሀይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ የአስተሳሰብ እድሳት፣ የአዲስ እቅድ ጅማሮ ፣ የስኬት መንደርደርያ፣ የጋብቻ እና የመብዛት ነጸብራቅ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም በአካባቢ ልማት፣ በግብርናና የንግድ ስራዎች የሚመክሩበት ወጣቶች በአባቶች የሚመረቁበት፣ አብሮነትን የሚንጸባረቅበት ነው ያሉት።

በመሆኑም የመስቀል በዓል የጉራጌ ማህበረሰብ ትውፊቱን የሚያሳይበትና ማህበራዊ መስተጋብሩን የሚያከናውንበት በመሆኑ ይበልጥ ማስተዋወቅ እና ማበልጸግ እንደሚገባ አቶ አበራ አስታውቀዋል።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት አመርጋ እንደገለጹት የመስቀል ክብረ በዓል ከሀይማኖታዊ ስርዓቱ ባለፈ እጅግ አስደናቂ የሆኑ የፍቅር፥ የአብሮነት፥ የአንድነት ፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴት የሚታይበት እንዲሁም የጋብቻ ስርዓት የሚፈጸምበት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በዓሉ ይበልጥ እንዲተዋወቅና ሽፋን እንዲያገኝ የጉራጌ ዞን አስተዳደር በየ አመቱ ፌስቲቫል አዘጋጅቶ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር እያደረገ መሆኑ ገልጸዋል።

ማህበረሰባችንም ከበዓሉ ጎን ለጎን ተፈጥሮዊ እና ባህላዊ የቱሪስት መዳረሻዎቻችን ማስጎብኘት፣ ማስተዋወቅና ማልማት ይገባዋል ነው ያሉት ወ/ሮ መሰረት አመርጋ።

በበዓሉ የተገኙት አካላት እንዳሉት በአሉ በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ክዋኔዎች የሚፈጸሙበት ሲሆን በአሉ ስናከብር የተቸገሩ በመርዳት፣ በመተሳሰብ እና በመቻቻል ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል።

በፌስቲቫሉ በርካታ መገናኛ ብዙሃን መታደማቸውን በመግለፅ የጉራጌ መገለጫ የሆኑ እሴቶች፥ የማህበረሰቡ ሰላም ወዳድነትና እንግዳ ተቀባይነት ዓርዓያነት ያለው በመሆኑ ለማስተዋወቅና ሌላውም እንዲማርበት ያስችላል ብለዋል።

በመድረኩም ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳ የተወጣጡ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና ሚዲያዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *