ሰኔ 19/2016ዓ.ም
በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስተር በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከ57 ሚሊዮን 44 ሺህ 8 መቶ ብር በላይ ወጪ የሚገነባው የመቆርቆር የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ።

በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌድሪ ውሃና ኤነርጂ ሚኒስተር አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ 13 ሺህ የዜጎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ።

የኢፌድሪ የውሃና ኤነርጂ ሚኒስተር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው በመሰረት ድንጋይ የማኖር ስነ ስርአት ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት በወረዳው እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበረሰብ የመጠጥ ውሃ ችግር መፍትሔ በመስጠት ረገድ ፋይዳው ትልቅ ነው።

ፕሮጀክቱ በኬንያ፣ በሱማሊያና ኢትዮጵያ ሀገሮች ውሃ አጠር በሆኑ አከባቢዎች የሚከናወን መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ በፕሮግራሙ ከታቀፉት 55 ወረዳዎች የምሁር አክሊል ወረዳ አንዱ ነው።

በወረዳው የሚገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ሲጠናቀቅ 13 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱ ማስፋፊያ ሲደረግ በአጠቃላይ 26 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በ57 ሚሊዮን 44 ሚሊዮን 801 ብር እንደሚገነባ ጠቁመው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከሚያደርገው ክትትል ጎን ለጎን የክልሉ መንግስት፣ የዞኑ አስተዳደር፣ የወረዳው ማህበረሰብ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

በቀጣይም በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የውሃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ዳዊት ኃይሉ የክልሉ ህብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል።

የውሃ መሰረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ የሚጠይቅ በመሆኑ ፕሮጀክቱን በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት ይገባል ብለዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብም የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ላይ የሚጠበቅባቸውን ትብብር ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት በዞኑ የዜጎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ለማሟላት በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ የልማት ድርጅቶችና ተባባሪ አካላት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

የዞኑ የንጹህ የመጠጥ ዉሃ ሽፋን 38 ነጥብ 28 በመቶ ላይ መሆኑን ያነሱት አቶ ላጫ በዚህም 562 ሺህ 313 የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን 813 ሺህ 33 የማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ የሚፈልግ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ የዞኑ የውሃ ሽፍን ለማሻሻል የዞኑ መንግስት ከሚሰራው ስራ ጎን ለጎን የፌደራልና የክልል መንግስት አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጠውም አስገንዝበዋል።

በምሁር አክሊል ወረዳ የሚገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የወረዳው ሽፋን ከፍ ከማድረግ ባለፈ በአካባቢው ከዚህ ቀደም የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደሚቀርፍም አመላክተዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ የወረዳው የውሃ ሽፋን 28ነጥብ 5 መሆኑንና በመቆርቆር ቀበሌ የሚገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ሽፍኑ ከፍ እንዲል ያደርገዋል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በቀበሌውና በአካባቢው የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ችግሩን እንዲቀረፍ በማድሩጉ አመስግነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *