ቀን ጥቅምት 28/2015 ዓ.ም

በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ የቸሃ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ሀገር ከሚገኘው Sahay slolar association ጋር በመተባበር በጉራጌ ዞን በቸሃ ወረዳ ለሚገኘው ለሸሬ ጤና ጣቢያ የሶላር ፓኔል ድጋፍ አደረገ።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሸምንሳ በድጋፉ ወቅት ተገኝተው እንዳሉት ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ለወረዳው ማህበረሰቡ በግብርናና በትምህርት ዘርፍ በርካታ ስራዎች ሲያከናዉን መቆየቱን ጠቁመው በጤናው ዘርፍም ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ለዚህም በወረዳው በሸሬ ቀበሌ የሚገኘው የሸሬ ጤና ጣቢያ ከዚህ በፊት የወረዳው መንግስት ለጤና ጣቢያው የትራንስፎርመር ገጠማ ቢያደረግም መቃጠሉን አስታዉሰዋል።

የወልቂጤ ዩንቨርሲቲ ይህንን የማህበረሰቡን ችግር በመረዳት ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበርና ክትትል በማድረግ ችግሩ እንዲቀረፍ ማድረጉን ጠቁመዉ ለዩኒቨርሲቲዉና ድጋፍ ላደረገዉ አጋር ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ጤና ጣቢያው ከ19ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ይሰጣል ያሉት አቶ ጥላሁን ከዚህ ቀደም የነበረው የእናቶች የወሊድ አገልግሎት፣ የህጻናት ክትባት ፣ ህክምና እና የላብራቶሪ አገልግሎት ችግር ሙሉ ለሙሉ በመቅረፍ ህብረተሰቡ ያለ ምንም እንግልትና ወጪ በአከባቢያቸው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋልም ብለዋል።

በወረዳው በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ህብረተሰቡን የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራም አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

በወረዳው በርካታ ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች የመብራት ተደራሽነት ላይ ሰፊ ውስንነት መኖሩን ገልጸው ይህ መሰል ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፣ ለዚህም የወረዳው መንግስት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አስታዉቀዋል።

በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ረዳት ፕሮፌሰር አበበ ያበኬር እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በዞኑ የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑባቸው አካባቢዎች በመለየት የተቋማቱ ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰራ ጠቁመው በዚህም በዛሬ እለት በቸሃ ወረዳ ለሸሬ ጤና ጣቢያ ከሳይ ሶላር አሶሴሽን ጋር በመተባበር የሶላር ፓኔል ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ፕሮጀክቱ የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ባልሆኑባቸው አከባቢዎች መሰል ስራዎች ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የሶላር ፓኔሉ ከ1 ነጥብ 7ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም ሶላር ፓኔሉ 3መቶ 50 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የትራንስፖርት ወጪ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ፕሮጀክቱ በሌሎችም አካባቢዎች የበለጠ ለማስፋት በሚደረገው ስራ የዞኑ መንግስትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የቸሃ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ከፋ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ጤና ጣቢያው የመብራት አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት ህብረተሰቡ ላላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዲዳረጉ ከማድረጉም ባለፈ ባለሙያዎች ተረጋግተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዳይሰጡ ማነቆ ሆኖ መቆየቱንም ገልጸዋል።

በተለይም የእናቶች የወሊድ አገልግሎት፣ የህፃናት ህክምና፣ የላብራቶሪ አገልግሎት ለማግኘት ታካሚዎች ወደ ወልቂጤ፣ ጉብሬና እምድብር ይላኩ እንደነበር ጠቁመው የሶላር ፓኔሉ ድጋፍ እነዚህ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀርፍም ተናግረዋል።

በቀጣይ በወረዳው በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *