መስከረም 8/2015ዓ.ም

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው 4ኛ ዙር 8ኛ አመት 22ኛ መደበኛ ጉባኤ ለ2015 በጀት አመት የቀረበለትን ከ5 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ የተለያያዩ ሹመቶችንም በማጽደቅና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ጉባኤውን አጠናቋል።

ለምክር ቤቱ የቀረበለትን የበጀት ረቂቅ ሰነድ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኃላ የ2015 በጀት አመት 5ቢሊየን 264ሚሊዮን 803ሺህ 565 ብር ሆኖ ጸድቋል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደሪ አቶ መሀመድ ጀማል በማጠቃለያ ንግግራቸው ወቅት እንዳሉት የዞኑ ማህበረሰብ የሚጠይቃቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ በመመለስ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ከመረጃ ክፍተት ጋር ተያይዞ ዞኑ ከክልል በሚደርሰው በጀት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቁመው በቀጣይም ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል።

አያይዘውም ወጪና ብክነት በመቀነስ የተበጀተውን የመንግስት በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን ህብረተሰቡ፣ አጋር ድርጅቶችና ባለሀብቶችን በማሳተፍና ዞኑ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሰራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወይዘሮ አርሺያ አህመድ በበኩላቸው የህዝቦች አንድነትና አብሮነት የበለጠ በማጠናከር በየአከባቢው የሚስተዋሉ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን እንዲፈቱ መስራት እንደሚገባም መክረዋል።

በምክር ቤቱ ውሎ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ለምክር ቤቱ አባላት እጩዎችን ያቀረበ ሲሆን በዚህም
1- የተከበሩ አቶ ኸይሩ መሀመድ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ
2- አቶ አብዶ አህመድ የጉራጌ ዞን ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊ
3- አቶ ሙራድ ረሻድ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ
4- አቶ ዘነበ ደበላ የጉራጌ ዞን ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አድርጎ በመሾምና የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ጉባኤው ተጠናቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *