እንኳን ደስ አላችሁ!
ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ባዘጋጀው 8ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር ላይ የሶስተኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል::
ዩኒቨርሲቲው መስከረም 08 ቀን 2014 ዓ.ም ከምስጋና ጋር የልህቀት ማዕረግ ተሸላሚነቱን የሚያረጋግጥ ዋንጫና የምስክር ወረቀት በታላቁ ቤተመንግስት በኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተበርክቶለታል::
በስፍራው ተገኝተው ይህንን ታላቅ ሽልማት የተቀበሉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል፣ የአካ/ጉ/ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሀብቴ ዱላ፣ የአስ/ኮር/ማ/ም/ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ገነት ወልዴ እና የተ/ጥ/ማ/ማ/ዳ/ ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ብዙዓለም አሰፋ ለመላው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና ለአካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ የ”እንኳን ደስ አላችሁ” መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
ዩኒቨርሲቲው በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የካቲት 12 ቀን 2012 ባዘጋጀው 7ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር ላይ ተሳትፎ የከፍተኛ አድናቆት የምስክር ወረቀት ሽልማት አግኝቶ የነበረ ሲሆን በዘንድሮው ዓመትም ባስመዘገበው የተሻለ አፈጻጸም የሽልማት ደረጃውን ከፍ በማድረግ የሶስተኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል:: ዩኒቨርሲቲው ላስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም ስኬት፣ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ እና እጅግ በሚያበረታታ መልኩ ለተገኘው ውጤት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ካውንስል፣ የተ/ጥ/ማ/ማ/ዳይሬክቶሬት የስራ ክፍልና ለውድድሩ አስፈላጊውን ግብዓት ያሰባሰቡ የቡድን አባላት፣ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ተማሪዎች እጅ ለእጅ ተያይዘው የተቋሙን ሁለንተናዊ አፈጻጸም በሚደግፍ ደረጃ ተቀናጅተው በመስራታቸው የተገኘ ትልቅ ስኬት በመሆኑ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋሲል ደሊል ለተገኘው የዋንጫ ሽልማት ለተቋሙ ማህበረሰብ ያላቸውን ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል::
በተጨማሪም ይህንን ውድድር ላዘጋጀው የኢትየዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ምስጋናቸውን አቅርበዋል:: በመጨረሻም በተገኘው ሽልማት ልንኩራራ ሳይሆን ይበልጥ ልንጠናከር፣ ልንዘናጋ ሳይሆን ያሉብንን ክፍተቶች ስልታዊ እቅድ በመንደፍ፣ ለላቀ ውጤትና ስኬት በትጋትና በቆራጥነት የስራ ወኔና መንፈስ ልንጓዝ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *