ሀምሌ 2/2014 ዓ.ም

የጉራጌ ዞን አስተዳደር 1443ኛው የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በአዲስ አበባ በመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ።

የዘንድሮ የአረፋ በዓል የጉራጌ ዞን አስተዳደር መቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ማዕከል በመገኘት ከ4 ሺ በላይ አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ማዕድ በማጋራትና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ተከብሯል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር አቶ መሀመድ ጀማል የዘንድሮ የአረፋ በዓል የትንሿ ኢትዮጵያ መገለጫ በሆነችውና የሀገር ባለውለታዎች፣ የነገ ተስፋ ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር በመቄዶንያ ከ4ሺ በላይ አቅመ ደካሞችና አዕምሮ ህሙማን ማዕድ በማጋራት ማክበራችን ታላቅ ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

በበዓሉም ማእድ ከማጋራት በተጨማሪ ለእነዚህ አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን 5 መቶ ሺህ ብር ለተቋሙ ግንባታ የሚውልና የተለያዩ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ፍራሾች፣ ብርደልብሶች፣ አንሶላዎችና ሌሎችም ድጋፎች ተደርጓል።

የአረፋ በዓል በዞኑ በመተባበር፣ በመተጋገዝ በጋራ የሚከበር በዓል ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ከቤተሰቦቻቸው የተራራቁ ቤተሰቦች ተሰብስበው በአካባቢያቸው ከማክበራቸውም ባለፈ በማህበራዊና በልማታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የልማት ስራዎችን የሚሰሩበትና ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን እምነት ሳይለዩ በመደገፍ በተለየ መልኩ የሚከበር በዓል ነው ብለዋል።

ከዞኑ ከ1 መቶ በላይ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን ከመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ጋር በመተባበር ወደ ማዕከሉ በማስገባት እንዲደገፉ ተደርጓል ነው ያሉት።

በመሆኑም ከተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ስፋት አንፃር በወልቂጤ ከተማ ማዕከሉ ለማስገንባት የ1ሄክታር መሬት ለማዕከሉ ማስረከባቸው ተናግረው ግንባታው እስኪ ጠናቀቅም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ አብድርከሪም ሼህ በድረዲን በበኩላቸው መረዳዳት፣ መተሳሰብ የኢትዮጵያን ባህል በመሆኑ የጉራጌ ዞን አስተዳደር የአረፋ በዓል ምክንያት በማድረግ ከመቄዶንያ አቅመደካማ አረጋውያንና እዕምሮ ምህሙማን ጋር በማክበር ያደረጉት በጎ ተግባር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያስቀጥለው ይገባል ብለዋል።

በማዕከሉ የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መልኩ መደገፍ እንዳለበት አመላክተው ህዝበ ሙስሊሙም በዓሉ ሲያከብር በየአከባቢው ያሉትን አቅመ ደካሞችን በመደገፍ መሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳ በበኩላቸው የጉራጌ ህዝብ አካባቢ ድንበር የማይወስነው በመሆኑ የአረፋ በዓልም በመቄዶንያ የአረጋውያንና አዕምሮ ማዕከል በመገኘት ከአቅመ ደካሞች ጋር ማክበራቸው ትልቅ መልዕክት አለው ብለዋል።

በመቄዶንያ ማዕከል የተሰበሰበው ተረጂ ማህበረሰብ በቋንቋ፣ በአካባቢ፣ በእምነት፣ በፆታና በማህበራዊ መሰረት ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በሚወክለው ማዕከል በዓሉ ማክበራቸው ለዞኑ አስተዳደር ምስጋና አቅርበዋል።

የመቄዶንያ ማዕከል ተረጂ አረጋውያን እንዳሉት የዞኑ አስተዳደር የአረፋ በዓል በመቄዶንያ በመገኘት ከአረጋውያንና አዕምሮ ህሙማን የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በማክበራቸው መደሰታቸውም ተናግረዋል።

በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!
= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *