ግንቦት 16/2014 ዓ.ም
ኬርኦድ የልማትና ስፓርት ማህበር ዘንድሮ ለሁለተኛ ዙር “ለኢትዮጵያ ሰላም እንሮጣለን” በሚል መሪ ቃል የሚያካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።
ዘንድሮ በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደው የ15 ኪሎ ሜትር የኬሮኦድ የጎዳና ላይ ሩጫ የዞኑ ባህልና እሴት ጎልቶ እንዲወጣ፣በሳላም እንዲጠናቀቅና ሩጫው ግቡን እንዲያሳካ ከሚመለከታቸው የዞኑ የመንግስት ስራ ሀላፊዎች፣ “የኬሮድ የልማትና ስፖርት ማህበር “የስራ ሀላፊዎች፣አመራሮችና አትሌቶች ጋር ዛሬ በወልቂጤ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
መጪው ሰኔ 19/2014 ዓ.ም ኬርኦድ የልማትና ስፓርት ማህበር” ዘንድሮ ለሁለተኛ ዙር በወልቂጤ ከተማ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወነ መሆኑ ተጠቁመዋል።
በውይይቱ የተገኙት የጉራጌ ዞን አስዳደር ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አሰፋ አካሉ እንዳሉት ፕሮግራሙ ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ያለምንም ችግር ታድመው እንዲመለሱ፣የዞኑ ባህልና እሴት ጎልቶ እንዲወጣና በአጠቃላይ ውድድሩ የታለመለት ግብ እንዲያሳካ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።
የዚህ ውድድር ዋና ባለቤት የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ነው ያሉት አቶ አሰፋ ከተማው ሆቴሎች ምቹ እንዲሆኑ፣የከተማው ሰላምና ፀጥታ የማጠናከር፣የከተማው የጽዳትና ውበት ማስጠበቅና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች የተቀናጀ ኮሚቴ አደራጅቶ መምራት አለበት ገልፀዋል።
የኬርኦድ የልማትና ስፓርት ማህበር ፕሬዝዳንት አትሌት ተሰማ አብሽሮ እንደገለፀው ስፓርት ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ከሚያደርገው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ተተኪ አትሌቶች ለማፍራት፣የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር፣የማህበረሰቡ ባህልና እና እሴቶች ለማስተዋወቅና የአካባቢ በጎ ገፅታ ለመገንባት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ።
ዘንድሮ ለሁለተኛ ዙር “ለኢትዮጵያ ሰላም እንሮጣለን” በሚል መሪ ቃል ሰኔ 19/2014 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ የ15 ኪሎ ሜትር ታላቅ የጎዳና ሩጫ ከዚህ አንፃር ስኬታማ እንዲሆንና ግቡ እንዲመታ የዞኑ መንግስት እገዛና ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።
እንደ ማህበር በ2013 አመተ ምህረት በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ውድድር ከተገኙ ልምዶች በመነሳት ጉድለቶችን በሚያርም ሁኔታ ሰፊ ዝግጅቶች መደረጋቸውና አሁን ባለበት ዝግጅቶቹም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ገልፀዋል።
በዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ ከ20 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ ስፓርተኞ አንደኛ ለሚወጣ 75 ሺህ ብር፣ሁለተኛ ደረጃ ለሚወጣ 50 ሺህ ብር እንዲሁም ሶስተኛ ደረጃ ለሚወጣ 30 ሺህ ብር ሽልማት ለመስጠት መዘጋጀቱን አትሌት ተሰማ አብሽሮ ጠቁሟል።
አምና በተካሄደው ሩጫ ተሳትፈው በደረጃ ያጠናቀቁ አትሌተች በውጭ አገር ተወዳድረው እንዲያሸንፉ ጥሩ ልምድ መፍጠሩንና በቀጣይም የውድድር አድማሱ በማስፋት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ታዋቂ አትሌቶች እንዲሳተፉ ለመጋበዝ እንደሚሰራም አትሌት ተሰማ አመላክቷል።
የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ በበኩላቸው ለ2ኛ ዙር የሚካሄደው የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ በወልቂጤ ከተማ የተሳካና ግቡ እንዲመታ ከተማው አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርግና የተሳካ ውድድር እንደሚካሄድ ገልፀዋል።
አክለውም አቶ አበበ ውድድሩ የተሳካ እንዲሆን ጠንካራ ኮሚቴ በማዋቀር ከከተማው ወጣቶች፣ከፀጥታ አካላት፣ከመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት፣ከንግዱ ማህበረሰብና ከመላው የከተማው ህዝብ ጋር የተቀናጀ ስራ ይሰራል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሀላፊ አቶ መስፍን ተካ ይህ የስፖርት ውድድር በዞናችን መካሄዱ ትልቅ እድልና ከመሪ ቃሉ ጀምሮ ስለ ሰላም የሚጣራ፣ሁሉም የሚያሳትፍና ወቅታዊ በመሆኑ የተቀናጀ የሰላምና ፀጥታ ዝግጅት ይደረጋል ብለዋል።
ይህ የልማትና ስፖርት ማህበር የሀገራችንን ስም ያስጠሩ አትሌት ኮማንደር ሰለሞን ባረጋ፣ አትሌት ሙክታር ከድር፣ አትሌትና አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ በጋራ አቋቁመው በየዓመቱ እንዲካሄድ ያስጀመሩት ሲሆን ዘንድሮ ለ2ኛ ዙር ሰኔ19 በወልቂጤ ከተማ እንደሚካሄድ በርካታ ሚዲያዎች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ መሰጠቱም ይታወሳል።
ዘንድሮ ለሁለተኛ ዙር በድምቀት የሚካሄደው የጎዳና ሩጫ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ እና አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ጨምሮ በርካታ ከአለም አቀፍና ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ታላላቅ አትሌቶችና የክብር እንግዶች ተገኝተው ሩጫውን እንደሚያስጀምሩትና እንደሚታደሙ ተገልጿል።
በውይይቱም የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አሰፋ አካሉ፣የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ አሰፋ ጨምሮ የዞን አመራሮች፣የዞንና ከተማ ፖሊስ አዛዦች፣ የኬሮድ የልማትና ስፖርት ማህበር የስራ ሀላፊዎች፣አመራሮችና አትሌቶች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።
በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!
= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN