የአረፋ በአል የአብሮነት፣የአንድነትና የመቻቻልን እሴት መሰረት እንደሆነም የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ። በጉራጌ ዞን በቸሀ ወረዳ በአብሬት ቀበሌ 1 ሺህ 4 መቶ 42ኛዉ የኢድ አል አድሃ የአረፋ በአል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል። በበአሉ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንዳሉት የዘንድሮ የአረፋ በአል ልዩ የሚያደርገዉ የውስጥና የውጪ ጫናዎችን በመቋቋም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሀ ሙሌት ባጠናቀቅንበት ብሎም በሀገራችን የህግ የበላይነት ለማስከበር ጥረቶ በሚደረግበት ወቅት የምናከብረው በአል በመሆኑ ነው ብለዋል። የአረፋ በአል የአብሮነት፣የአንድነትና የመቻቻልን እሴት መሰረት እንደሆነም የተናገሩት አቶ መሀመድ በዞኑ ህዝቦች ዘንድ እጅግ በደመቀ፣ በልዩ ጥበብና በተለየ ስሜት የሚያከብሩት የአረፋ በአል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያየ የሚገናኝበት፣ ታላላቆች የሚከበሩበት፣ አንድነት የሚደምቅበትና ፍቅር የሚሞቅበት እንደሆነም አብራርተዋል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተዉ የሚሰሩ የዞኑ ተወላጆች በርካታ ኪሎ ሜትሮች አቋርጠዉ ወደ ትዉልድ ቄያቸዉ በመምጣት በመሰባሰብ በአሉን ያከብሩታል ብለዋል። የአረፋ በአል ጠላትን ድል በማድረግ ለፈጣሪ እጅ የመስጠትና በታማኝነት የመገዛት መገለጫ ነዉ ያሉት አቶ መሀመድ አባታችን ነቢይላ ኢብራሂም (አ.ሰ) ልጃቸውን እስማኤል እንዲሰው ከፈጣሪ በደረሳቸው ትዕዛዝ መሰረት የሰይጣንን ጉትጎታ ተቋቁመው ውድ ልጃቸውን ለመስዋእት አቅርበው የፈጣሪን ትዕዛዝ በፍፁም ቁርጠኝነት ሊፈፅሙ ሲሉ አላህ በምትኩ ሙክት በግ ቀይሮላቸዋል። አባታችን ነብዩ ኢብራሂም(አ.ሰ) እና ልጃቸዉ እስማኢል የሰይጣንን ክፋትና ጉትጎታ ድል እንዳደረጉ ሁሉ እኛም ዛሬ በህዝብ ውስጥ ጥላቻን ቂም-በቀልን መለያየትን መነቋቆርን ለሚሰብኩ የተዛባ መረጃ በማቀበል ለዘመናት በፍቅር በመተሳሰብ አብሮ በኖሩ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር በማህበራዊ ሚድያና ባገኙት አማራጭ ሁሉ እየተጉ ላሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ድል መንሳትና እኩይ አላማቸውን ማምከን ያስፈልጋል ብለዋል። የአረፋ በአል የይቅር ባይነትና የፍቅር መታሰቢያ ተምሳሌትም እንደሆነ ተናግረዉ አባታችን አደም(አ.ሰ) እና እናታችን ሀዋ የፈጣሪን ትዕዛዝ በመጣስ ከጀነት ወደ ምድር ሲወረወሩ የተለያየ ቦታ በመውደቃቸው ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአላህ እዝነትና ይቅር ባይነት አረፋ ላይ ተገናኝተዋል እኛም ዛሬ ፈጣሪ እዝነት ከገባንበት ችግር ሁሉ የምንወጣበት በአል እንዲሆን ተመኝተዋል ። የእለቱ የክብር እንግዳ የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ አብድልከሪም ሼህ በድረዲን እንዳሉት በተለያዩ ምክንያት ወላጆቻቸዉን ያጡና የተቸገሩ ሰዎች በማቀፍና አንድላይ በማክበር የአረፋ በአል በሰላም በፍቅር በዱአ ማሳለፍ ይገባል ብለዋል። አሁን ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ የዉስጥና የዉጭ ወራሪዎች እየተፈታተዋት እንደሆነም የሚታወቅ ነዉ ያሉት ሼህ አብድልከሪም አንድነትን ከመቸዉም ጊዜ በላይ ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል። ለ1 ሺህ 4 መቶ 42ኛ ጊዜ የሚከበረዉን የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ዘንድሮ ለየት የሚያደርገዉ 6ኛዉ ሀገር አቀፍ ምርጫ በተሳካበት ወቅት በመሆኑና የታላቁ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተከናወነበት ቀን መሆኑ ተናግረዋል። የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ፈለቀ ሀይሌ በበኩላቸው 1 ሺህ 4 መቶ 42ኛዉ የኢድአል አድሃ አረፋ በአል በጉራጌ ዞን ባህላዊ ይዘቱ ሳይለቅ ለትዉልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ነዉ። የአረፋ በአል በጉራጌ ብሔር ማህበረሰብ ዘንድ ማህበራዊ እሴቶች የሚጎለብትበትና ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች የእምነት ተከታዮች ጋር በመሆን ሰብሰብ ብለዉ በአሉን በደስታ ያከብሩታል ብለዋል። በበአሉ አከባበር ላይ በመገኘት የእንኳን መጣቹ መልዕክት ያስተላለፉት የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር በበኩላቸዉ የዘንድሮ የኢድ አል አድሃ አረፋ በአል በታሪካዊ የአብሬት ሀድራ በሚገኝበትና በየአመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለፀሎትና ዱአ በሚሰበሰቡት ቀበሌ መከበሩ ለየት ያደርገዋል ብለዋል። ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በአል ሲያከብር ከኮቪድ 19 እራሱን በመጠበቅ፣ ለሀገራችን ሰላም በመጸለይ እንዲሁም ለተቸገሩ ወገኖች ማዕድ በማጋራት መሆን አለበት ገልፀዋል። አቶ ሙራድ አክለውም ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችና የቱሪዝም መስህቦች ባለቤት መሆንዋ አስታውሰዋል።በመሆኑም በቸሃ ወረዳ አብሬት መስኪድ እና በውስጡ ከ80 አመት በላይ ተጠብቆ የቆዩ የተለያዩ ቅርሶች መኖራቸው ገልፀው ይህ የአብሬት ሀድራና በውስጡ የሚገኙ ቅርሶች ለቱሪስት መስብነት እንዲውሉና በቅርስነት እንዲመዘገቡ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።በበአሉ የተገኙት አንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች በሰጡት አስተያየት የአረፋ በአል የተራራቁ ቤተሰብ የሚገናኝበት ፣ አብሮ የመብላት ባህል የሚጎለብትበት፣ አቅም ለሌላቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚረዱበትና በአሉ በጋራ የሚያከብሩት እንደሆነም አስታዉቀዋል።ዘንድሮም በአሉ ሲያከብሩ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህላቸው በማጠናከር ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ዱአ እያደረጉ እንደሚያከብሩትም ገልፀዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *