የመና አካባቢ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንዲለማ በማድረግና የማህበረሰቡ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የመንገድ ግንባታ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

ዘመናት የአካባቢው ማህበረሰብ ጥያቄ የነበረውን የመና አካባቢ የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ በመጀመሩና ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

በጉራጌ ዞን እኖር ወረዳ መና አካባቢ እየተሰራ ያለው የመንገድ ከፈታ ስራና ስፍራው ላይ ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት የወረዳው አመራሮች በተገኙበት የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።

የእኖር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ግርማ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የመንገድ ግንባታው የተጀመረበት አካባቢ ከጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ከመሆኑ አንፃር ቦታው ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለማዕድን ዘርፍና ለሌሎችም የልማት ስራዎች እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያለበት ስፍራ መሆኑን ጠቁመው ይህንን ስፍራ በቀጣይ በማልማት ለመጠቀም በወረዳው ውስን በጀት የመንገድ ከፈታ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

አክለውም በእኖር ወረዳ የመና አካባቢ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እንዲለማና ማህበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን የመንገድ ግንባታና ከፈታ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት በአካባቢዉ የመንገድ ስራ ባለመሰራቱ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርት ለማምረት ይሁን ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት ይቸገሩ እንደነበር ጠቁመው አርሶ አደሩ የሚጠይቃቸው የልማት ጥያቄ መሰረት በማድረግ የመንገድ ከፈታ ስራው ተጀምሯል ብለዉ ለመንገዱ ከፈታ ስራ 1ሚሊየን ብር በእቅድ እንደተያዘና እስካሁን ድረስ 6 መቶ 25 ሺህ ብር ወጪ መደረጉም ገልፀዋል።

የመና የተፈጥሮ ሀብት ያለበት ስፍራ ለማልማትና የአከባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል ብለዉ ስፍራዉ በተገቢዉ በማልማት ወረዳውና ዞኑ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የዞንና የክልሉ መንግስትና የአከባቢው ባለሀብቶች ለስፍራው ልዩ ትኩረት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል።

የእኖር ወረዳ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ሙሸዲን አህመድ በበኩላቸው የመንገድ ስራው የአከባቢው ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄ መሆኑን ገልፀው በወረዳው አመራር ቁርጠኝነት የመንገድ ስራው መጀመሩንም አስታዉቀዋል።

የመንገድ ከፈታ ስራው ሲጠናቀቅ አርሶ አደሩ በእንሰሳት እርባታና ድለባ፣ በንብ ማነብ እንዲሁም በግብርና ስራቸዉም ምርትና ምርታማነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፋይዳዉ የጎላ መሆኑም ጠቁመዋል።

በቀጣይም መንግስት፣ የአካባቢው ማህበረሰብና የተወላጅ ባለሀብቶች አቅም በመጠቀም አካባቢው በማልማት የሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በተጨማሪ የአካባቢው ማህበረሰብ ብሎም የወረዳውና የዞኑ የኢኮኖሚ ገቢ እንዲያድግ የክልሉና የዞኑ መንግስት ለአከባቢው ትኩረት ሊሰጡት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የእኖር ወረዳ ትራንስፖርትና መንገዱ ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን ኑርጋ በበኩላቸዉ የመንገድ ግንባታው አላማ ለዘመናት ሳይለማ የቆየውን ስፍራ በማልማት በስፍራው ያለውን ማዕድን በመጠቀም የወረዳው የመንገድ ጥራት ችግር እንደሚቀርፉ ጠቁመው የመሬት ሀብቱ በአግባቡ በመጠቀም ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝምና ለግብርና ልማት ስራዎች ለማዋል ያለመ ነው ብለዋል።

የተጀመረው የመንገድ ስራ ዞኑ ከኦሮሚይ ክልል በቀጣይ ለማስተሳሰር በ10 አመት መሪ እቅድ መታቀዱን ገልፀው የመንገድ ስራው 30 ኪሎ ሜትር ቢሆንም መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ለማሰራት ከፍተኛ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ በዘንድሮ አመት የወረዳው ውስን በጀት በመጠቀምና የ90 ቀን እቅድ መሰረት በማድረግ የ7 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህም በመጀመሪያ ዙር እስካሁን የ5 ኪሎ ሜትር የከፈታ ስራ መሰራቱን የገለፁት ኃላፊው በሁለተኛው ዙር የ2 ኪሎ ሜትር የመንገድ ከፈታ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

አቶ አህመዲን ሸሪፍ፣ አቶ ሙከረም ነጋሽና አቶ ደንድር ኮላ የአከባቢው ነዋሪዎች ሲሆኑ በጋራ በሰጡት አስተያየት የዘመናት የአካባቢው ማህበረሰብ ጥያቄ የነበረውን የመንገድ መሰረተ ልማት በመጀመሩና ጥያቄያቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት አካባቢው ላይ መንገድ ባለመሰራቱ ምክንያት ከብት ለማሰማራት፣ ለምርት የሚሆኑ ግብአቶችን ለማስገባትና ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማቅረብ ይቸገሩ እንደነበር ገልፀው መንገዱ ለመስራት በመጀመሩ በቀጣይ በተለያዩ የልማት ስራዎችን ላይ በመሰማራት የገቢ አቅማቸዉን ለማሳደግ እንደሚሰሩምና አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *