የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል ህብረተሰቡ የላቀ ሚና መጫወት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ

የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል ህብረተሰቡ የላቀ ሚና መጫወት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አሳሰበ።የመምሪያው የ11 ወራት እቅድ አፈጻጸም የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ መካሄዱን ተመልክቷል።የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፋሲካ አለሙ ባለፉት 11 ወራት ህብረተሰቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።በዞኑ የቅድመ ወሊድ ክትትል የሚያደርጉ እናቶች ቁጥር እያደገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ፋሲካ እርግዝናቸው ካረጋገጡ እናቶች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በጤና ተቋም የቅድመ ወሊድ ክትትል ያደረጉ ሲሆን በሰለጠነ የጤና ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት ያገኙ እናቶች ቁጥር ደግሞ ከ76 በመቶ በላይ እንደሆነ አስረድተዋል።አምራች፣ ጤናው የተጠበቀ እና ብቁ ዜጋ ለማፍራት ጥራቱን የጠበቀ ክትባት ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ ፋሲካ ባለፉትት 11 ወራት የቢጫ ወባ፣ የፖሊዮ፣ የኩፍኝ ወረርሽኝና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች አስቀድሞ ለመከላከል የክትባት አገልግሎት መስጠት እንደተቻለም አስረድተዋል። በመሆኑም የዞኑ የክትባት ሽፋን 98 በመቶ ሲሆን ጥራቱን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል አቶ ፋሲካ ።የጤና ተቋማት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ህብረተሰቡ በተቋማቱ አፈጻጸም ላይ አስተያየት ከመስጠት ጀምሮ ክፍተቶቹን ለመሙላት ህብረተሰቡ ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን ሚና ሊወጣ ይገባል ብለዋል።አያይዘውም ኃላፊው በጤና ተቋማት የሚስተዋሉ የመረጃ ጥራት መጓደል፣ የቲቢ ህሙማን ልየታ አናሳ መሆኑ፣ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻል ትኩረት የሚሹ ተግባራት በመሆናቸው በቀጣይ የተቋማቱ የቦርድ አባላትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።የኮቪድ19 በሽታ የሚያሳድረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስና ስርጭቱን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎችና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው በቀጣይ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ስርጭቱን ለመከላከል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።አቶ መሀመድ አሚን ጀማል የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲሆኑ የህብረተሰቡ ጤና ለማሻሻል የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞች ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ ባለሞያዎቹ በሁሉም ቀበሌዎች ተደራሽ እንዲሆኑ መስራት ይገባል ብለዋል።በወረዳው የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞች ማሳካት እንዳልተቻለ የተናገሩት አቶ መሀመድ አሚን ፓኬጆቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጋቸው በህብረተሰቡ ጤና መጎልበት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረዋል ብለዋል። በመሆኑም በቀጣይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ተዟዙረው የሚሰሩበት ስርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።የእነሞርና ኤነር ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እርስቱ ደምስስ በበኩላቸው በበጀት አመቱ እናቶችና ህጻናት ሞት ከመቀነስ በተጨማሪ ነፍሰጡር እናቶች በሰለጠነ የጤና ባለሙያ የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።እንደ አቶ እርስቱ ገለጻ በወረዳው ሞዴል ቀበሌ ለመፍጠር እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ የሚሰጡት የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።አክለውም አስተያየት ሰጪዎቹ በምክክር መድረኩ የቀረቡ ጠንካራ አፈጻጸም ለማስቀጠል እና ክፍተቶቻቸው በማረም ለየህብረተቡ ጤና ለማጎልበት እንሰራለን ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *