መጋቢት 10/ 2014 ዓ.ም

የትምህርት ባለድርሻ አካላቶች ተቀናጅተዉ በመስራት የተማሪዎች ዉጤት እንዲሻሻልና በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት እንዲመጣ አጽእኖት ሰጥተዉ መስራት እንዳለባቸዉ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አሳሰበ።

በእዣ ወረዳ የሚገኙ መምህራን ፣ሱፐር ቫይዘሮችና ርዕሰ መምህራኖች ፣ መምህራን ማህበርና ሌሎች የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላቶች በተማሪዎች ዉጤት መቀነስና ስነ ምግባር ላይ ዉይይት አካሄደዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ እንዳሉት የተማሪዎች ዉጤትና ስነምግባር ለማሻሻል ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት ይገባል።

ተማሪዎች በቂ እዉቀት እና ክህሎት አግኝተው በክልላዊና ሀገራዊ ፈተናዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከማድረግ አንጻር ችግሮች መኖራቸዉም ተናግረዉ በቀጣይ ችግሮቹን ለመፍታት ከቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ብለዋል።

በዘንድሮ አመት የክልላዊና ሀገራዊ ፈተና ለሚፈተኑ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከወዲሁ የተለያዩ አይነት ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራም እንደሆነም አብራርተዋል።

ከሌሎች ዞኖች አንጻር በዞኑ ዝቅተኛ ዉጤት እንደተመዘገበም የተናገሩት አቶ አስከብር በ2013 ዓመተ ምህረት የ8ኛ ክልል አቀፍ ፈተና 64 ነጥብ 5 ፐርሰንት ተማሪዎች ብቻ ማሳለፍ መቻላቸዉም አስረድተዉ ይህም በክልሉ ካሉ ዞኖች ዝቅተኛ ዉጤት የተመዘገበበት እንደሆነም አስታዉሰዋል።

የ2013 አመተ ምህረት የ12ኛ ክፍል ዉጤት እየተነተኑ እንደሆነም ጠቁመዉ በዚህም ተማሪዎች በሚጠብቁት ደረጃ ዩኒቨርሲቲ ማስገቢያ ዉጤት ማምጣት እንዳልቻለም አስረድተዋል።

በዋናነት የተማሪዎች ዉጤት ማሽቆልቆል እንደምክንያት ያነሱት ተማሪዎች ፍላጎት ኖሯቸዉ ትኩረት ሰጥተዉ አለመማርና የትምህርት አመራሮች ብቃት፣ ክትትልና የሀላፊነት ስሜት ተላብሶ በተጠያቂነት ያለመስራት ችግር መኖሩም ተናግረዋል።

ችግሩ በሚፈጥሩ የትምህርት አመራሮች ፣ መምህራኖች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ያለመዉሰድ ችግሮች መኖሩም ተናግረዉ መምህራኖች ላይ የሚስተዋሉ የብቃት፣ የተነሳሽነት እንዲሁም የዝግጅትና ተማሪዎችን ለማብቃት የትጋት ችግር መኖሩም አስረድተዋል።

የትምህርት አመራሩ ፣ መምህራንና ማህበረሰቡ የተማሪዎች ዉጤትና ስነ ምግባር ላይ በቅርበት ከመከታተል አንጻር ለትምህርት ቤቶች ለግብአት አቅርቦት ከሚያደርገዉ ያህል የተማሪዎች ዉጤትና ስነ ምግባር እንዲሻሻል ከማድረግ አንጻር ልዩ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ችግሮች መኖሩም አስረድተዋል።

በዞኑ ባለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት በተማሪዎች ዉጤት ላይ ዝቅተኛ ዉጤት እያስመዘገቡ ያሉ ሙህር አክሊል ፣እዣ ቸሃ ፣ጉመርና፣ጌታ ወረዳዎች ሲሆኑ እነዚህም ወረዳዎች ለመደገፍ እቅድ በማቀድ እየተመዘገበ ያለዉን ዉጤት ለማሻሻል እየተሰራ ነዉ ብለዋል።

በመድረኩ የተገኙት የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ እንዳሉት ከተማሪዎች ዉጤት ማሻሻልና ስነ ምግባር ላይ ተጨባጭ ለዉጥ ለማምጣት መስተካከልና መታረም ያለባቸዉ ነገሮች ተለይተዉ ቀርበዋል።

በትምህርቱ ዘርፍ የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመጣ በቀጣይ በ8ኛ እና በ12ኛ ክፍል የተማሪዎች ዉጤትና ስነምግባር በወረዳዉ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲሻሻል ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ ሊሰራበት እንደሚገባም አስረድተዋል።

በዉይይት መድረኩ የተገኙ አንዳንድ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች በሰጡት አስተያየት ተማሪዎች ብቁ ከማድረግ አንጻር ችግሮች መኖራቸዉ ተናግረዉ ይህንንም ችግር ለመፍታት አጽእኖት ሰጥተዉ እንደሚሰሩም አስታዉቀዋል።

በተማሪዎች ዉጤት ማሽቆልቆል ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ ተቀናጅተዉ በመስራት የተማሪዎች ዉጤትና ስነ ምግባር ለማሻሻል በትምህርቱ ዘርፍ የሚፈለገዉን ዉጤት እንዲመጣ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *