የካቲት 05/2014 ዓ.ም

መንግስት የህግ የበላይነት በማስከበር የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ ማስፈን እንደሚጠበቅበት የቆሴ ከተማ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጠየቁ።

በቆሴ ከተማና ዙሪያው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከጉራጌ እና ከሀዲያ ዞን የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በቆሴ ከተማና አካባቢው በሚኖሩ በሀድያ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው በማህበራዊ እና በሜይንስትሪም ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸው የእኖር ኤነር ወረዳ አስተዳደር ገለጸ።

ቆሴ ከተማ፣ ባረዋና ዳያስ ቀበሌዎች በጉራጌ ዞን በእኖር ኤነር ወረዳ የሚገኙ ሲሆን የጉራጌና የሃድያ ብሄረሰቦች በትዳር እና በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ተሳስረው እና ተጋምደው የአካባቢው ልማት በጋራ የሚጠቀሙ የማህበረሰብ ክፍሎች ይገኙባቸዋል ።

እነዚህ የጋራ እሴት ያላቸው ብሄረሰቦች ሰላም ለማደፍረስ የግል ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በኢመደበኛ አደረጃጀት ከለውጡ ወዲህ በመሰማራት ዛቻና ማስፈራራት ያደርሱባቸዋል።

በአካባቢው ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ነዋሪዎቹ በሰላም የመኖር መብታቸው ተጠብቆ የእለት ተዕለት ተግባራቸው ለማከናወን በአካባቢው መንግስት የህግ የበላይነት እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

አብሮ መብላት፣ በትዳር መዛመድ እና አካባቢን በጋራ ማልማት ከቀደሙት አባቶች የወረሱት እሴት ማስቀጠል ሲገባ ጥቂት ግለሰቦች የህብረተሰቡን አንድነትና ሰላም ለማደፍረስ የሚያደረጉት እንቅስቃሴ እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በመሆኑም የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች ይህንን እኩይ ተግባር በመኮነን በአካባቢው ሰላም ለማስፈን ከመንግስት ጋር ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ11ኛ ሻለቃ አድማ ብተና እና ልዩ ሀይል አዛዥ ኮማንደር ሙስጠፋ በሽር እንደገለፁት ቆሴ አካባቢ ያለው ችግር አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከሰተ ቢሆንም ችግሩ በዘላቂነት ለመፍታት ከጉራጌ እና ከሀዲያ ዞን አመራሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በመሆኑም የአካባቢው ሰላም በሚያደፈርሱ አካላት ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከሁለቱም ዞን የጸጥታ መዋቅሮች መርማሪ ቡድን በማቋቋም ምርመራ እየተደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በአካባቢው የመንግስት መዋቅር እንዳይኖርና የህብረተሰቡን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሠላም አካላት ህብረተሰቡ የማይወክሉ በመሆናቸው የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች ሊገስጿቸውና ወንጀለኞች በአካባቢው እንዳይሸሸጉ በማድረግ መንግስት በወንጀለኞች ላይ የሚወስደው እርምጃ ውጤታማና ፈጣን ለማድረግ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የእኖር ኤነር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሸምሱ ሸሀቡ በበኩላቸው በሀገሪቱ የተፈጠረው ለውጥ ተከትሎ በእኖር ኤነር እና አምካ ወረዳዎች አጎራባች ቀበሌዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ነዋሪዎቹ የሠላምና የደህንነት እጦት ተዳርገው እንደቆዩ ገልጸዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን በአካባቢው ሰላም እንዳይሰፍን በማድረግ የግል ጥቅማቸውን በሚያሳድዱ አካላት ነዋሪዎቹ ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ጥቃት እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ በቆሴ ከተማና አካባቢው በሚኖሩ በሀድያ ብሄረሰብ ተወላጆች ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው በማህበራዊ እና በሜይንስትሪም ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሸምሱ በአካባቢው ችግር እንደተፈጠረ ተደርጎ የሚለቀቁ ምስሎች በሌላው አለም የተከሰቱ ሁነቶችን በማቀነባበር እየተለቀቁ መሆኑን ህብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል ብለዋል ።

በየትኛውም የሚዲያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሙያዊ ስነምግባር ተላብሰው ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ተዓማኒነት ያላቸው መረጃዎች ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

መንግስት የህግ የበላይነት በማስከበር በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የጀመረው ጥረት ከግብ ለማድረስ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *