1445ኛው የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክንዋኔዎች በድምቀት ተከበረ።

ሰኔ 9/2014 ዓ

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉ በሚያከብርበት ወቅት ምስኪኖችና የተቸገሩ ወገኖች በመርዳት ልናከብር ይገባል ሲሉ ያነጋገርናቸው የወልቂጤ ከተማ የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ።

የአረፋ በዓል በኢትዮጵያ በተለይም በጉራጌ ዞን በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ አበይት ክብረ በዓላት አንዱ ሲሆን የተራራቁ ወገኖች የሚቀራረቡበት፣ የተቸገሩት የሚረዱበት ህዝቡ የአብሮነት እሴቶች የሚያጎለብቱበት በዓል ነው።

በወልቂጤ ከተማ የበድረዲን መስጂድ ኢማም ኡስታዝ አብድልጀሊል ህያር በኢድሶላት ወቅት እንዳሉት በበዓሉ ከሚታረደው እርድ አንድ ሶስተኛው ለሚስኪኖችና ለአቅመ ደካሞች በማካፈል የሚከበር የአንድነትና የመተሳሰብ በዓል ነው።

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ከአላህ የታዘውን ተግባር በመፈጸም የተቸገሩ ወገኖችን ከማሰብ ባለፈ በማካፈል ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በሀገር ሰላም፣ ልማትና እድገት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣም ይገባል ነው ያሉት።

የበዓሉ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኢድአል አደሃ (አረፋ) የኢድ ሶላት በሰላም በድምቀት መከበሩ ተናግረዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በበዓሉ ወቅት የመረዳዳት የመተሳሰብ እሴቶችን በማጠናከር ምስኪኖችን በማሰብና በማካፈል መከበር እንዳለበትም ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *