ፍትሃዊ የንግድና የግብይት ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የሸማቹ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የ2016 በጀት ዓመት ጉባኤው በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በጉባኤው ላይ እንዳሉት በሀገሪቱ የተደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት በማድረግ የገበያ ዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግና ህገ- ወጥ የንግድ ስርዓት እንዳይስፋፋ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

በሀገር ውስጥ በሚመረቱ የግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማስወገድና የኑሮ ውድነት ለመቀነስ እንዲቻል በሁሉም አካባቢ የሰንበት ገበያ ከሰንበት እስከ ሰንበት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ የማጠናከር ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ህብረተሰቡ የሚያማርሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ ፍትሃዊ የንግድና የግብይት ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ የሸማቹ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ላጫ ጋሩማ አስገንዝበዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የንግድ ስርዓቱ በማዘመን የንግዱ ማህበረሰብ ባለበት ቦታ ያለምንም እንግልት ፍቃድና እድሳት እንዲፈጽም 17 የነጥብ ጣቢያዎች በማቋቋም የኦንላይን አገልግሎት በጥሩ ሁኔታ እየሰጠ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም በዞን ደረጃ ያልነበረ የንግድ ዘርፍ ማህበርና የነጋዴ ሴቶች ማህበር በማቋቋም ነጋዴው ማህበረሰብ አቅሙን እንዲያሳድግና ችግሮች ሲኖሩ በጋራ ተወያይቶ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ተደራጅቶ ወደ ስራ የገባ ቢሆንም አባላት የማፍራት ስራ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የሰንበት ገበያ በዞኑ በሁሉም አካባቢ ተግባራዊ በማድረግ አምራችና ሸማች በቀጥታ ተገናኝተው ግብይት እንዲፈጽሙ በማድረግ ህገ ወጥ ደላላ መቀነስ የተቻለ ሲሆን በወልቂጤ ከተማ የተጀመረውን ከሰንበት እስከ ሰንበት የገበያ አገልግሎት በሁሉም አካባቢ እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡

የህገ-ወጥ ግብረ ሀይል በዞኑ በሁሉም አካባቢ ተደራጅቶ ወደ ስራ በመግባቱ በ2016 በጀት ዓመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብስብ ለመንግስት ፋይናንስ ገቢ መደረጉን የገለጹት የመምሪያው ኃላፊ በህገ ወጦች ላይ አስተማሪ እርምጃ ከመውሰድ አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶች በተያዘው በጀት ዓመት ሊቀረፍ ይገባል፡፡

በዞኑ በኤክስፖርት ምርቶች 9 ሺህ 245 ነጥብ 25 የዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የተቻለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በውስን ምርቶች የተወሰነውን የኤክስፖርት ምርት በማስፋት ሽምብራ፣ ባቄላ፣ የቢራ ገብስ፣ በሎቄና ሰሊጥ መላክ የተጀመረ መሆኑን በመገንዘብ በህገ-ወጥ መንገድ ግብይት እንዳይፈጸም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስግብግ ነጋዴዎች በሸማቹ ማህበረሰብ ላይ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ በሚያደርጉት ላይ መንግስት አስተማሪ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ጊዜ ያለፈባቸው ምግቦችና መድሃኒቶች ለህብረተሰቡ በማቅረብ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በሚያደርጉ ህገ ወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ በ2016 በጀት አመት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተሻለ አፈጻጸም በማሳየቱ አንደኛ በመውጣት የዋንጫና ሰርተፊኬት እንዲሁም ኮንፒውተርና ላፕቶፕ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን ዛሬ ባካሄደው ጉባኤ ይህንን ውጤት እንዲመጣ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የዞን ተቋማት፣ የወረዳዎችንና የከተማ አስተዳደሮች የንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤቶች የዋንጫና የሰርተፊኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በመጨረሻም በ2017 በጀት ዓመት ሊፈጸሙ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራት ላይ የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ ከወረዳና ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር የግብ ስምምነት በመፈራረም ጉባኤው ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *