ፍትሀዊ የትምህርት ተደራሽነት ለማረጋገጥ የባለሀብቶች ተሳትፎ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገለጸ።

መስከረም 22/2015

ፍትሀዊ የትምህርት ተደራሽነት ለማረጋገጥ የባለሀብቶች ተሳትፎ የላቀ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገለጸ።

በቸሀ ወረዳ በኢንጂነር ጥበቡ ስለሺ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ስለሺ ሰማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር የአንድን ሀገር ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ትምህርት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ባለሀብቶች እና ማህበረሰቡ በንቃት መሳተፍ አለባቸዉ ብለዋል።

የወረዳው ማህበረሰብ በትምህርት ተቋማት ግንባታ ላይ ያለው ግንዛቤ የዳበረ በመሆኑ ዜጎች ፍትሀዊና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ያለፉት ሶስት አስርት አመታት በትምህርት ተደራሽነት ማረጋገጥ ላይ ብቻ መሰራቱ ብቁ፣ ተወዳዳሪና በራሱ የሚተማመን ትውልድ በመቅረጽ ረገድ ከፍተኛ ጉድለት እንደነበረበት አቶ ሙራድ አውስተዋል።

በመሆኑም የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የአካባቢው ባለሀብቶችና ማህበረሰቡ በማስተባበር ደረጃውን የጠበቁ የቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለምረቃ የበቃው ስለሺ ሰማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነገው ሀገር ተረካቢ ህጻናት የተሻለ እውቀት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ትምህርት ቤቱንም ላስገነባው ለኢንጅነር ጥበቡ ስለሺ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ወላጆች ልጆቻቸው በእውቅት ታንጸው እንዲያድጉ በማድረግ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ የራሳቸው አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ወደ ትምህርት ቤት መላክ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተማረ ለማ በበኩላቸው መንግስት ባለው ውስን ሀብት የትምህርት ተቋማት በሚፈለገው ደረጃ ማስፋፋት የማይችል በመሆኑ ማህበረሰቡና ባለሀብቱ በትምህርት ተቋም ግንባታ ላይ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በወረዳው ለመማር ምቹ ሁኔታ ያላገኙ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በመኖራቸው ባለሀብቶች በእውቀት የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢንጂነር ጥበቡ ስለሺ የሶው ኢን ሆፕ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን አስተባባሪ ሲሆኑ በቸሀ ወረዳ አስተፖ ቀበሌ የተገነባው ስለሺ ሰማ የቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ህጻናት ከአካባቢያቸው ሳይርቁ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ትምህርት ቤቱ አሁን ላይ ግንባታቸው የተጠናቀቀ አምስት ብሎኮች ያሉት ሲሆን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎላቸዋል። የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው ሶው ኢን ሆፕ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን ከተሰኘው አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት መሆኑን ገልጸዋል።

በ2015 የትምህርት ዘመን 64 ህጻናት ተቀብሎ እንደሚያስተምር የገለጹት ኢንጅነር ጥበቡ ትምህርት ቤቱ በየ አመቱ 64 ተማሪዎች እየተቀበለ እስከ 8ኛ ክፍል ለማስተማር ይሰራል ብለዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የመማሪያ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ቢሮ፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ቤተ መጽሐፍት እና ቤተ ሙከራ እንደሚኖሩት የተናገሩት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ለዚህ ፕሮጀክት እስከ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ተመድቦለታል ብለዋል ።

ሳይማር ያስተማረን ህዝብ ማገልገል መቻል እድለኛነትም ጭምር በመሆኑ የሚያደርጉት የበጎ አድራጎት ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቤቱ መገንባት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት በአቅራቢያቸው እንዲማሩ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል ።

ከዚህ ቀደም በአቅራቢያቸው የቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው ለመራቅ ይገደዱ እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ ስለሺ ሰማ የቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት እድሜያቸው ሳይባክን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *