ጎጎት (የጉራጌ ህዝብ የአንድነት ቃል_ኪዳን)

ነሐሴ11/2014 ዓ.ም

ጎጎት (የጉራጌ ህዝብ የአንድነት ቃል_ኪዳን)

በዘመነ መሳፍንት የጉራጌ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የጦርነት ዕጣ ደርሶት ጎጥ ለይቶ ወንዞችና ጅረቶችን ከልሎ ከአጎራባች ብሔረሰቦችና እርስ በርሱ ይዋጋ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በዘመኑ የእርስ በርስ ጦርነት ያላካሄደ ቤተ-ጉራጌ የለም።

የውጊያው መሰረታዊ ዓላማ በዘመነ መሳፍንት በሀገሪቱ ህዝብ መካከል ይካሄድ ከነበረው የእርስ በርስ ውጊያ የተለየ አልነበረም። አንዱን ጎሳ በአንዱ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀትና አንዱ ቤተ ጉራጌ የአንዱን የመሬት ይዞታ ለማድረግ የጦርነት ዓይነተኛ ዓላማ እንደነበር ይታወቃል።

አጼ ሚኒሊክ ግዛታቸው ለማስፋፋት ጦራቸውን ወደ ተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች ባቀኑበት ወቅት ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች በመካከላቸው የነበሩትን ቅራኔዎችና የእርስ በርስ ግጭቶቻቸውን አስወግደው የንጉሱን የግዛት ማስፋፋት ወረራ የተከላከሉ መሆናቸው ታሪክ ያስረዳል።

ድንበር ከልሎ በጎሳ ተቦዳድኖ እርስ በርሱ ይዋጋ የነበረው የጉራጌ ህዝብም “ሁለት ውሾች በአንድ አጥንት ይጣላሉ ጅብ ሲመጣባቸው ግን አብረው ይመክታሉ።” እንደሚባለው ሁሉ የእርስ በርሱ ግጭት በማስወገድ በጋራ የመከላከል ውጊያ የመጣበትን የባዕድ ኃይል መክቷል።

የግጦሽ መሬት ለማግኘትና የሌላውን ድንበር ለመግፋት በሚደረጉት የእርስ በርስ ግጭቶች የሚፈጠረው እልቂት አላስፈላጊ ከመሆኑም በላይ ትውልድን አመናምኖ በባዕድ ሀይል መጠቃትን እንደሚያስከትል በማስገንዘብ በየቤተ-ጉራጌ የጦር አበጋዞችና የጎሳ መሪዎች የሰላም ጥሪ ያቀረቡ መሆናቸው ይነገራል።

ከእነዚህ መካከል ጥሪ የሰመረለትና ለተግባር የበቃለት የሶዶ ክስታኔ ጉራጌ ተወላጅ የሆነው አቶ ሰላ ኦዳ ነው።

ይህ ሰላም ወዳዱ አቶ ሰላ ኦዳ ከሶዶ ክስታኔ ቤተ-ጉራጌ በመነሳት በመስቃን፣ በስልጤ፣ በዳሎቻ፣ በወለኔ፣ በዶቢ፣ በኡልባረግ፣ በእነቆርና በጠቅላላው ሰባት ቤት ጉራጌ በመዘዋወር ለከፍተኛ የጦር አበጋዞችና ለጎሳ መሪዎች የእርስ በርስ ውጊያ ለጉራጌ ህዝብ የማይጠቅመው መሆኑን አስረድቷል።

የዚህ ሰው ጥሪ በአብዛኛዎቹ ቤተ-ጉራጌዎች ተቀባይነት በማግኘቱ የመጀመሪያው የጉራጌ ህዝብ የአንድነት ስምምነት ጉባኤ በዶቢና በሞህር ድንበር ዘቢደር ላይ ተካሂዷል። ይህ የስምምነት ጉባኤ “ጎጎት” በሚል መጠሪያ ይታወቃል።

በዚህ የመጀመሪያ ጉባኤ አንዱ ቤተ-ጉራጌ ሌላውን እንዳይወርና እንዳይዘርፍ ስምምነት ላይ ተደረሰ። ይህንን ስምምነት ያላከበረ ወገን የጋራ እርምጃ እንዲወሰድበት ተወሰነ።

በጉባኤው የታሰረው የአንድነትና የሰላም ቃል ኪዳን በየቤተ-ጉራጌው ሙሉ ድጋፍ በማግኘቱ የእርስ በርሱ ውጊያ ቆሞ በጉራጌ ህዝብ ዘንድ መቀራረብና መተሳሰብ ፈጠረ።

ሁለተኛው የጎጎት ጉባኤ ሁሉም ቤተ-ጉራጌዎች በሚያክለው ቦዠባር ላይ ሲካሄድ ሶስተኛው ጉባኤ ደግሞ በጌታ-ጉራጌ ልዩ ስሙ አታዞ በተባለው ስፍራ ላይ መካሄዱን ለማወቅ ተችሏል።

እነዚህ ሶስት የጎጎት ጉባኤዎች በጉራጌ ህዝብ መሀከል አለመግባባቶችን አስወግደው ወንድማማችነትን አሰፈኑ።

አንዱ ቤተ-ጉራጌ ሌላውን እንዳያጠቃ ቃል ኪዳን አስተሳሰሩ። ህዝቡ እርስ በርሱ ከመጋጨትና በጦርነት ከመፈላለግ ይልቅ በትጋት ሰርቶ በሰላም መኖር አብሮ በመኖር ላይ እንዲያተኩር አቅጣጫውን አመለከቱ።

ዛሬ የጉራጌ ብሄረሰብ ሰላም ወዳድና ስራ አክባሪ ህዝብ መሆኑን እየተጠቀሰ የሚነገርለት ሰናይ ባህሉ የቀድሞ አባቶች እንደ ጎጎት የመሳሰሉ ስምምነቶች በጣሉት መሰረት የተገነባ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በዶቢ፣ በቦዠባርና በአታዞ ላይ የተካሄዱት የጎጎት ስምምነቶች በህዝቡ መሀከል የነበሩት አለመግባባቶች በማስወገድና ቅራኔዎችን በመፍታት ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በእነዚህ ተከታታይ የስምምነት ጉባኤዎች መሰረት የጣለው የጉራጌ ህዝብ አንድነት በ1928 ዓ/ም እነቆር ላይ በተካሄደው ” ታላቁ ጎጎት” በባህላዊ ቃል-ኪዳን ( በጉዳ ወይም በጉርዳ) እንዲጠነክር ተደረገ።

እነቆር ላይ የተደረገው የአንድነት ስምምነት “ታላቁ ጎጎት” ተብሎ እንዲጠራ ያስቻሉት ብዙ ምክንያቶች አሉ። እነዚህም፦
1, በጎጎት ስብሰባ የተሳተፉ ቤተ- ጉራጌዎች ቁጥር ከምንም ጊዜ በላይ በርከት ብሎ መገኘቱንና በስምምነቱ ሌሎች ብሄረሰቦችንም ያካተተ መሆኑ፤
2, ጉባኤው የውስጥ ችግሮችን በማቃለል ላይ ከመወሰን አልፎ የውጭ ወረራን በጋራ መከላከል ስለሚቻልበት ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወያየና ያስማማ በመሆኑ፤
3,እያንዳንዱ ቤተ-ጉራጌ የዘር ሀረግ ትስስሩን በመቃኘት ማንነቱን ለተቀረው ወገኑን ያስተዋወቀበት ጉባኤ በመሆነ፤
4,በሌሎች የጎጎት ስብሰባዎች ያልታየና ያልተደረገው የጎጎት ውሳኔዎችን በበላይነት የሚቆጣጠር አካል የተሰየመለት ጉባኤ በመሆኑ የእነቆሩ የአንድነት ስምምነት “ታላቁ ጎጎት” ተብሎ ይጠራል።

ይህ ጉባኤ ተጠናክሮ ሊቀጥል ያልቻለበት ምክንያት የጎጎት አባቶች በህይወት ባለመኖራቸው በአመራር አካል እጦት እየተዳከመ ቢመጣም ቃል ኪዳኖቹ ጸንተው እስከ ዛሬ ድረስ በጦርነትና በድንበር ግጭት የሚፈላለግ ቤተ-ጉራጌ የለም።

አሁን በስራ ላይ የሚገኘው የጉራጌ ባህል አስተዳደር ሸንጎ በ2013 ዓ.ም ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። ይህ የባህል አስተዳደር ሸንጎ የጉራጌ አንድነት ለማጠናከር ጽህፈት ቤት ከመክፈት ጀምሮ አመታዊ ጉባኤ በማካሄድ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ለበለጠ መረጃ በጉራጌ ህዝብ ታሪክ ላይ የተዘጋጀው የጎጎት መጽሐፍ እንዲያነቡ እንጋብዛለን።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ
Twitter:- https://4pvf.short.gy/bTJNNn

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *