ያሉንን ጸጋዎቻችን ለይተን በማልማት ሀብት ፈጥረን ህብረተሰባችን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የወልቂጤ የመሰረተ ልማት ክላስተር የሱፐርቪዥን አባላት ገለጹ።

በጉራጌ ዞን በመሰረተ ልማት ክላስተር ሴክተር መስሪያ ቤቶች ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።

የክልሉ የሱፐርቪዥን አባላት የመስክ ምልከታውን አስመልክተው እንደተናገሩት ዞኑ ያሉትን ጸጋዎች ለይቶ ማልማት ቢችል ከዞኑ ባለፈ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ የሚበቃ ሀብት ይገኛል።

በዞኑ በርካታ በመስኖ ሊለማ የሚችል ለም መሬት እና የውሃ አለኝታ ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን አርሶ አደሮችና ወጣቶች አደራጅቶ በሙሉ አቅማቸው ወደ ልማት እንዲገቡ በማድረግ የህብረተሰቡ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ይህንንም ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን በማምረት አበረታች ስራ እየሰሩ መሆናቸውን በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን የሱፐርቪዥን አባላት ተናገሩ።

በዞኑ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ክምችት እንደሚገኝና ይህንንም በአግባቡ ጥናት በማድረግ ለልማት እንዲውል በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ተገልጿል።

የቦዠባር የምንጭ ውሃ የወልቂጤ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳለው የጠቆሙት የሱፐርቪዥኑ አባላት ከፌዴራል ጀምሮ የከተማው የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል ይሰራል ብለዋል።

በወልቂጤ ከተማ መናኸሪያ የተጀመረው የኢቲኬቲንግ የክፍያ ስርዓት በሁሉም አካባቢ መስፋት ያለበት ጥሩ አሰራር ቢሆንም አሽከርካሪዎች ከመናኸሪያ ከወጡ በኋላ ተጨማሪ ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና ትርፍ በመጫን ህብረተሰቡ በሚያማርሩ አሽከርካሪዎች እና የስነ ምግባር ጉድለት በሚስተዋልባቸው የትራፊክ ፓሊሶችና የመንገድ ደህንነት አስከባሪዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ የሱፐርቪዥን አባላት አሳስበዋል።

የከሬብና የመጌቻ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች፣ የወልቂጤ የደረቅ ጭነት መናኸሪያ ግንባታዎች መጓተት እንዲሁም በብድር ገብተው ከሁለት አመት በላይ በመብራት አቅርቦት ችግር ምክንያት ወደ ስራ ማስገባት ያልተቻሉ የሊዝ ማሽኖች በዞኑ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እየፈጠሩ በመሆናቸው ችግሩ ለመቅረፍ ክልሉ ከዞኑ ጋር በመሆን ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል።

በወልቂጤ ከተማ እየተፈጸመ ያለውን የባጃጅ መቀማማት የጸጥታ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የጉራጌ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ በማድረግ ላይ የሚገኙ ጥሩ የልማት ስራዎችና ከፍተኛ ሀብት መፍጠር የሚያስችሉ ጸጋዎች መኖራቸውን የሱፐርቪዥን አባላት ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *