ያሉንን የውሃ አማራጮች ተጠቅመን የመስኖ ስራን አጠናክሮ በመስራት የአርሶ አደሩ ኑሮ መቀየር እንደሚያስፈልግ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል አስታወቁ።

በ2014 አመተ ምህረት በ1ኛ እና በ2ኛ ዙር በተለያዩ አትክልትና የሰብል አይነቶች 50ሺ 7መቶ 93 ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገለጸ።

መምሪያው የ2013 አመተ ምህረት የመስኖ ልማት አፈጻጸም ግምገማና የ2014 አመተ ምህረት የመስኖ ንቅናቄ መድረክ የዞን፣የወረዳ አመራሮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደተናገሩት ያሉንን የውሃ አማራጮ ተጠቅመን የመስኖ ስራን አጠናክሮ በመስራት የአርሶ አደሩ ኑሮ መቀየር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአርሶ አደሩ ኑሮ እንዲለወጥ ወቅቱን የሚመጥን ስራ መስራት ያስፈልጋል ያሉት አቶ መሀመድ ጀማል በዘርፉ ከዚህ በፊት እያጋጠሙን የነበሩ ችግሮችን በመለየት በመስኖ ስራዎች ላይ የሚጠበቀው ውጤት ለማምጣት በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች በመስኖ ልማት ዘርፍ የስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ለማድረግ መስራት እንዳለበት ገልፀዋል።

ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ እና የተበላሹትም ጥገና እንዲደረግላቸው በየደረጃው ካሉ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን በ2014 አመተ ምህረት በ1ኛ እና በ2ኛ ዙር በተለያዩ የሰብልና አትክልት አይነቶች 50 ሺ 7መቶ 93 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቀዷል ብለዋል።

በዋና ዋና ሰብሎች ለአብነትም ጎመን፣ድንች፣ ፓፓያ፣ ካሮት፣ቆስጣ ፣ማንጎ፣አቦካዶ እና በሌሎች አትክልትና ፍራፍሬዎች 2014 ዓም 50ሺ 793 ሄክታር መሬት ለማልማትና 13 ሚሊየን 8መቶ 92ሺ 735 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተጥሎ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የመስኖ ስራ የሀገራችን የምግብ እጥረት ለመቀነስ ጉልህ ሚና እንዳለው ህብረተሰቡ ተገንዝቦ በቀጣይም ለዘርፉ በሰው ኃይል እና በሎጀስትክ በመደገፍ፣አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ፓምፖች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ፣ልምድ ልውውጥ በማካሄድ፣የተለያዩ ግብአቶችን በማሟላት እንዲሁም በክላስተር በመስራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

አቶ ሸምሱ አክለውም የመስኖ ስራ ውጤታማ ለማድረግ የግብርና ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና የመስጠት፤ ተጨማሪ የውሃ ፓምፖችን የማሰራጨትና ግብአቶች የማሟላት ስራ በአፈጣኝ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍለ ማርያም መኩሪያ የንቅናቄ ሰነዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት በዘንድሮው የመስኖ ተግባር 2መቶ 23ሺ 7መቶ 2 አርሶ አደሮች፤ ወጣቶች እና ሴቶች ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ብለዋል።

በንቅናቄው መድረክ በመስኖ ተግባር ስራ የፓምፖች ብልሽት፣ የግብአት፣የቴክኖሎጂ እጥረት ፣ገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ያለማምረትና የገበያ ትስስር አለመፍጠር ፣አርሶ አደሩ በመስኖ ስራ ላይ የግንዛቤ ማነስ እንዲሁም ያሉትን የውሃ አማራጮች ተጠቅሞ ያለማምረት እና ሌሎችም ያጋጠሙ ችግሮች እንደ ነበሩ ተነስቷል።

አቶ ደሴ አበጋዝ ከሶዶ አቶ ሻፊ ሁሴን ከምስራቅ መስቃን በንቅናቄው መድረክ ከተገኙት ውስጥ ሲሆኑ በወረዳቸው አርሶ አደሮቹ ዝናብ ብቻ ተጠቅመው ከመስራት ወጥተው ባላቸው የውሃ አማራጭ በመስራታቸው በኑሮአቸው ለውጥ እያመጡ እንደሚገኙ አሳውቀዋል።

ለመስኖ የሚሆኑ ግበአቶች ቅድሚያ በሟሟላት በተለይም ሞተር ፓምፖች የመጠገን፣የተደፈኑ ካናሎች የመክፈት እና ግበአቶችን በመሟላቱ በወረዳቸው የመስኖ ስራ ለውጥ እያመጡ እንደሆነ ተናግረው ያላቸው የሰው ሀይል እና የውሃ አማራጭ እንደምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው እየሰራን ነው ብለዋል።

በእለቱም በዞኑ በመስኖ ስራ ላይ የተቀመሩ ምርጥ ተሞክሮዎች ለይታ ቀርበዋል ።

በመድረኩም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል፣የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ለማ ጨምሮ የመምሪያ ሀላፊዎች ባለሙያዎች፣የወረዳ አመራሮች፣የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተጠሪዎች ዩኒየኖች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *