ዩኒየኑ አባል ማህበራት ለማጠናከርና በቀጣይ ተግባራት ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ህብረት ስራ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት ወንበርጋ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ አድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን አጠቃላይ ተቋማዊ የስራ እንቅስቃሴው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ነው፡፡

የዩኒየኑ ህልውና የተመሰረተው በአባላት ኩፖን ሽያጭ ላይ ብቻ እንደተመሰረተ ደርጎ የሚታሰበው እሳቤ የተሳሳተ ስለሆነ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሁሉም አባል መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ምህረት ገልጸዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኙ የህብረት ስራ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በላይ የፖለቲካ አመራር ድጋፍ የሚያገኝበት ወቅት መሆኑን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጠንካራ ዩኒየንና የህብረት ስራ ማህበራት ለመፍጠር ከባለድርሻ ተቀናጅተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ያላቸውን ሀብት በአግባቡ በመጠበቅና ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኙ በሚችሉ ተግባራት ላይ መሳተፍ እንዲችሉ አደራጅ መስሪያ ቤት ችግር ፈቺ ድጋፍና ክትትል ሊያደርግ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ምህረት በተያያዘው በጀት ዓመት መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት በግብይት ላይ በመሳተፍ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል፡፡

የአድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራአስኪያጅ አቶ አበበ አመርጋ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ዩኒየኑ የሚስተዋሉበት ችግሮች በመቅረፍ ከዚህ ቀደም በጥሩ አፈጻጸም የሚታወቅበትን ስም ለመመለስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ ግብዓቶች ምርጥ ዘርና የሰብል መጠበቂያ ኬሚካሎች በማቅረብ፣ ማዳበሪያ የመጋዘን አገልግሎት በመስጠት ለህብረተሰቡ በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆን በማስቻል ምርት እንዲጨምር የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ ስራአስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

በአድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ንብረት የሆነው የቸምና የኑግ ዘይት ፋብሪካ የተቋቋመው ለአባላት ከተሸጠ የኩፖን ሽያጭ ከተገኘ ገቢ ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የፋብሪካው ወጪ የተሸፈነው ከባንክ ከተገኘ ብድር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በወቅቱ ፋብሪካው ለማቋቋም ጥቅም ላይ ከዋለው 36 ሚሊዮን ብር ውስጥ ከኩፖን ሽያጭ መሰብሰ የተቻለው 6 ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን ቀሪው ከባንክ ብድር መሆኑን የገለጹት አቶ አበበ ዩኒየኑ አሁንም በርካታ ሀብት ያለው ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚሰራ ተቋም እንደሆነ በመገንዘብ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በትኩረት ይሰራል፡፡

በቀጣይ በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ይዞታ የሆኑ መሬቶች ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ በማውጣት የመሬት ባለቤትነታቸው ሊያረጋግጡ እንደሚገባ አቶ አበበ አሳስበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በመድረኩ አድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በትክክል አሁን ያለበት ቁመና እንዲረዱ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸውና ይህንንም ለህብረተሰቡ በማስታወቅ በዩኒየኑ ላይ ያለውን እምነት በማሳደግ አዳዲስ አባላት ለማፍራት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል፡፡

አክለውም መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት የሚስተዋልባቸው የአደረጃጀትና የአሰራር ክፍተቶች ለመቅረፍ የሚያስችል ድጋፋዊ ክትትል አደራጅ መስሪያ ቤት ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *