የ6ኛ ክፍል ዞን አቀፍ የመጀመሪያ ደረጃ የእርከን ማጠቃለያ ፈተና በክላስተር ማእከል እንደሚሰጥ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ገለጸ።

የስድስተኛ፣ የስምንተኛና የአስራሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች የምዘና ሂደት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት የ6ኛ ክፍል ዞን አቀፍ የመጀመሪያ ደረጃ የእርከን ማጠቃለያ ፈተና ለመጀመሪያ ጊዜ በክላስተር ማእከል የሚሰጥ ይሆናል።

በዘንድሮ አመት የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ከሚማሩበት ትምህርት ቤት ወጣ ብሎ በተመረጡ የክላስተር ማዕከላትና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲፈተኑ ለማስቻል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

ይህም ከፈተና ዝግጅትና ፈታኝ መምህራን ከመመልመል ጀምሮ የምዘና ስርዓቱ በማዘመን ኩረጃ በማስቀረት በራሱ የሚተማመን ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃፊው ተናግረዋል።

አክለውም የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ብቁ ተማሪዎች ወደ ሚቀጥለው የክፍል ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል የምዘና ሂደት ተግባራዊ ለማድረግ ተማሪዎች በቅርብ እርቀት በክላስተር ማእከል እድሜያቸው ባገናዘበ እርቀት ሄደው እንዲፈተኑ ወላጆች ይሁንታን እንዲሰጡና ተማሪዎችም የስነልቦና ዝግጅት እንዲያደርጉ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በሰፊው እየተሰራመሆኑ አቶ አስከብር ወልዴ ገልጸዋል።

በመሆኑም ይህ ግብ እንዲሳካና ጥራት ያለው ምዘና ለመተግበር የተጀመረው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ሀላፊው ጠይቀዋል።

በጉራጌ ዞን ትህርምት መምሪያ የፈተና ዝግጅት አስተዳደርና የትምህርት ምዘና ዳሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም እንደገለጹት አዲሱ ስርዓተ ትምህርት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው የምዘና ስርአቱ ማሻሻል ነው።

በመሆኑም በዞናችን የምዘና ስርአቱ ለማሻሻልና ተማሪዎች በእውቀት በክህሎትና በአመለካከት ብቁ ለማድረግ በተገቢ ለመመዘን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።

መምሪያው ያለፉት አመታት ልምዶች በማጠናከር በ2015 ዓ.ም በ1ኛ ሴምስተር የ12ኛ፣ 8ኛ እና 6ኛ ክፍል ዞን አቀፍ ፈተና በማዘጋጀት ተማሪዎች ያሉበት ደረጃ በመገምገም በ2ኛ ሴምስተር ለድጋፍ ውለዋል።

በዚህም መሠሰረት በ2ኛ ሴምስተር የ6ኛ ክፍል ዞን አቀፍ የእርከን ማጠቃለያና የ8ኛ ክፍል ሞዴል ፈተና ተዘጋጅቷል።እነዚህ ፈተናዎች በዞናችን በቀጣይ ወቅት ለሀገር አቀፍ ፈተናዎች ውጤታማ ተማሪዎች ለማዘጋጀት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

እንደ አቶ መብራቴ ገለጻ በቀጣይ የሚሰጡ የክልልና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በጥራትና በብቃት ለመምራት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በትኩረት መሰራት አለባቸው ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዊች መካከል የማረቆ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ ስርጎታ በሰጡት አስተያየት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ለውጥ ከተደረገባቸው ነገሮች አንዱ የተማሪዎች የምዘና ስርዓት በማስተካከል ከኩረጃ የጸዳ እንዲሂሆን ለማስቻል ነው ብለዋል።

ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ቀንሙሉ ትምህርት ሆነው ላይብረሪ እንዲጠቀሙ ከምገባ ጀምሮ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪያችን የወልቂጤ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደምስ ፈቃደ በበኩላቸው የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል ከመምህራን፣ ከወላጆችና ከተማሪዎች ጋር በመወያየት ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በ2014 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል የገጠመውን የተማሪዎች ውጤት ስብራት ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች ከትምህርት ማህበረሰብ ጋር በመሆን እየተሰሩ ይገኛል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኪሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *