“የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጓል” ሲሉ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ገለጹ።

ጥር 9/2015 ዓ.ም

“የጥምቀት በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት ተደርጓል” ሲሉ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ ብጹዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ገለጹ።

የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ዜና ማርቆስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ብጹዕ አቡነ መልከ ፄዴቅ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለብርሃነ ጥምቀቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ የጥምቀት በዓል ነው።

የጥምቀት በዓል ጌታችንን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማሪያም ተወልዶ 30 አመት ሲሞላዉ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት እለት መሆኑን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል ።

በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ የአዳምና የሄዋን የእዳ ደብዳቤ ቀልጦ የጠፋበት፣ የስላሴ አንድነትና ሶስትነት የተገለጸበት ልዩ በዓል ነው።

ይህን ዕለት መሰረት በማድረግ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው በምዕመናንና በካህናት ታጅበው ወደ ጥምቀተ ባህር በማምራት በዓሉን የተመለከቱ ልዩልዩ መንፈሳዊ ክዋኔዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።

ይህ በዓል ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ባለፈ የመላው ኢትዮጵያዊያን በዓል ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት በትምህርት፣ በሳይንስና በባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ መሆን ችሏል። በዓሉን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል ።

በዓሉ በድምቀት መከበሩ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ቁጥር እንዲበራከት ከማድረግ ጎንለጎን በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በመሆኑም በዓሉ በልዩ ድምቀት ለማክበር ህዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ወጣቶች፣ ካህናትና ሌሎች የእምነቱ መሪዎች አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል።

መላው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለይም በልዩ ልዩ መልክ የተደራጁ የወጣት ማህበራት ኅብረት፣ ለበዓሉ ድምቀት በሁለንተናዊ ሥራ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶችና የሰ/ት/ቤት አባላት ከጸጥታ አካላት ጋር በመናበብ እና በጋራ በመስራት የክብረ በዓሉን መንፈሳዊ ድባብ ማስጠበቅ አለብን ብለዋል።

በዓሉ የእዳ ደብዳቤ የተቀደደበት፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ ፍቅርና ሰላም የወረደበት እለት በመሆኑ እኛም ከቂም፣ ከበቀል፣ ከጥላቻ ተላቀን ፍቅር፣ አንድነት፣ ይቅርባይነትን ተላብሶ ማክበር የይገባል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!
በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *