የግጭት በር ሲዘጋ የሰላም በር ተከፈተ!!


ባህል የአንድ ማህበረሰብ አኗኗር፣ አመጋገብ፣ አለባበስ፣ አጊያጌጥ፣ ሰርግ፣ ሀዘን… ወዘተ ሰብስቦ የያዘ ሀብቱ ነው ።

የቀደሙቱ አበው ይህንኑ ተፈጥሮ የገለጠችላቸው ሀብት በክፉና ደግ ጊዜያት መጠቀም ይችሉ ዘንድ በዘርፍ ዘርፍ ሰንደው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ ዛሬ ላይ ደርሷል።

በትውልድ ቅበብሎሽ ከአባቶች የተረከብነው ውብ የባህል እሴታችን ከዘመናዊ የህግና የፍትህ ስርዓት ሳይጣረስ እርቅ ለመፈጸም፣ ፍትህ ለማስፈን፣ አጥፊ ወይም በዳይ ለመገሰጽ ፣ ተበዳይ ለመካስ፣ ለመረዳዳት እየተገለገልንበት እንገኛለን።

ባህል ያልገዛው ለመሆኑ ምን አለ? የሰው ልጅ የሰላም አየር መተንፈስ ሲያቅተው እርስ በርስ ለአሸናፊነት የህይወት መስዋዕትነ ይከፍላል። መንግስት ደግሞ ህግ አስከባሪ አሰማርቶ ግጭት ለማርገብ ሲል ህግ ወደ ማስከበር ለመግባት ይገደዳል። በዚህ ሂደት ግን ግጭቱ ይርገብ እንጂ የቀደመው የህብረተሰቡ ሰላምና የአብሮነት እሴት ማምጣት እንደማይቻል በጉረጌ ዞን በመስቃንና በማረቆ የህብረተሰብ ክፍሎች የነበረው ግጭት ለዚህ አጭር ጽሁፍና እንደ አብነት ጠቅሰነዋል።

የመስቃንና የማረቆ የህብረተሰብ ክፍሎች በብዙ መለኪያዎች ተለያይተው የማይለያዩ፣ ተጣልተው የማይጣሉና ተራርቀው የማይራራቁ በትዳር የተጋመዱ በሀይማኖት የተሳሰሩ ወንድማሞች ናቸው። ከብዙ ቅዱሳን ጥቂት እርኩሳን አይጠፉምና እነዚህ በብዙ መንገድ እንደሚከብሩ የገመቱ እነኛ የፀብ ጠንሳሾች የተሳሰሩ ወንድማማቾች አለያይተው የግል ጥቅም ሲያሳድዱም ተመልክተናል።

ግጭቱ ድፍን ሶስት አመት አስቆጠረ ። በዚህ ግጭት ምክንያት 86 ንጹሃን በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው አጥተዋል። የእነዚህ ንጹሃን ደም ሰላም ፣ አንድነት ወይም ፍቅር ሳይሆን ያመጣው ከ7ሺህ 600 በላይ አባወራዎች ከቀዬያቸው መፈናቀልን ነው። ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ሲመጣ ጫናው እጅግ በረታ።

እነዚያ ተፈናቃዮች በአካባቢያቸው የሰላም አየር በነበረበት ወቅት በአመት ሁለትና ሶስት ጊዜ እያመረቱ በምግብ ራሳቸው ከመቻል አልፈው ለገበያ በማቅረብ በአርአያነት ይጠቀሱ የነበሩ ቢሆንም ለሶስት አመታት የደጋግ እጆች የሚጠብቁ ተመጽዋች ሆኑ ። በመስኖ ይለማ የነበረው መሬት ዳዋ ዋጠው።

የወረዳዎቹ ነዋሪዎች የሚያስፈልጋቸውን ልማት ሆነ መልካም አስተዳደር የሌላቸው እስኪመስል ድረስ መንግስት እለት ተዕለት የግጭት እሳት በማጥፋት ስራ ተጠምዶ ነበር።

በዚህ በክፉ ጊዜ በለው ቁረጠው እያሉ የጭካኔ መርዝ እየረጩ የመሳሪያ ሽያጭ በማጧጧፍ ገንዘብ ሲሰበስቡ የነበሩ የዘመኑ ከሀዲያን በአንድ በኩል መንግስት ግጭቱ ላይ ብቻ እንዲያተኩር በማድረግና ህዝቡ ደግሞ በልማትና በመልካም አስተዳደር እጦት በመንግስት ላይ እንዲያምፅ ማድረግ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ግጭቱ በማፋፋም መሳሪያ እንዲሸጡና ከፀቡ ትርፍ ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ ሰላም እንዲሰፍን ፈጽመው አልወደዱም ነበር።

እውነት ብትቀጥንም አትጠፋምና በውሸት የታወሩ ጥቅመኞች ፍላጎት ከእነዚህ ወንድማማቾች የባህል እሴት ፈጽሞ የማይጣጣም እንደሆነ የተረዱ የሀገር ሽማግሌዎች 29 ጊዜ ቢሰበሰቡም እርቁ ይሁንታን አላገኘም ነበር።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከጉራጌ ዞን አስተዳደር ጋር ሆነው ጊዜው ወስደው ግጭቱ ሊፈታ በሚችልበት መንገድ ጊዜው መከሩ። እሩቅ ተጓዥ እርምጃው ከአንድ ይጀምራል እንደሚባለው የእነዚህ ወንድማማቾች ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የመጀመሪያ እርምጃ ያደረጉት በሁለቱም ወገን ገለልተኛና ከዚህ ቀደም በሽምግልና ተሳትፎ ያልነበራቸው የሀገር ሽማግሌዎች መምረጥ ነበር። ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ እነኝህ የሀገር ሽማግሌዎች በነጻነት እንዲወያዩ እድል ተፈጥሮላቸው በአጭር ጊዜ ተሰፋ ሰጪ ውጤት ታየ።

ጎን ለጎን መንግስት የእነዚህ አባቶች ደህንነት በመጠበቅ እና በወረዳዎቹ ህግ የማስከበር ስራ መሰራቱ ለውጤት አብቅቷል።የግጭት መንገድ እየጠበበ፣ የጸብ ግድግዳ እየፈረሰ ሲመጣ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው የሚመለሱበት ደረጃ ላይ ተደረሰ።

እልልታው ቀለጠ፣ እንባ ያራጨ፣ ማቆሚያ ያልተገኘለት ለቅሶ በቆሼና በእንሴኖ ከተማ ተፈጠረ።ለሶስት አመታት ተቆርጦ የቀረ የሚመስለው የእነዚህ ወንድማማቾች ትስስር ዳግም ለማጠናከርና በግጭት ወቅት በሞት፣ በንብረት ውድመት፣ በአካል መጎዳትና በመፈናቀል የተፈጠረው የሞራል ስብራት ለመጠገን መለኞቹ የሀገር ሽማግሌዎች ከቀደሙት አበው ያወረሷቸው ቱባ ባህል ተጠቅመው እነዚህ ወገኖች በእርቅ ብቻ ሳይሆን ፍቅሩን፣ አንድነቱ፣ ሰላሙ ዳግም ላይደፈርስ በጉዳ ገምደው አጠነከሩት።

ይህ የጉዳዩ ስርዓት የተፈጸመው ሁለቱም ወገኖች ወጠጤ ጥቁር ፍየል በማረድ ነበር ግጭቱ በእርቀ ሰላም የደመደሙት።

አንደኛው ወገን የፍየሉን አንገት ይዞ ” ከእንግዲህ እንዚህ ወገኖች የሚያጋጭ፣ ሰላም የሚነሳ ፣ ደም የሚያቃባ ጸብ ጫሪ ያለ እንደሆነ እድሜው እንደዚህ ጥቁር ፍየል ደሙ ይፍሰስ ” እያለ አርዷል።

ሁለተኛ ወገን ደግሞ “እነዚህ ወንድማማቾች ያጣላ፣ ሰላማቸው ያደፈረሰ፣ ጸብ የጫረ እንደዚህ ጥቅር ፍየል ሆዱ ይቀደደ፣ ሆድ እቃውም የዘርገፍ” እያለ የፍየሉን ሆድ ቀደደ።

ከሁለቱ ወገን የተመረጡ ሁለት ሽማግሌዎች የእግራቸው አውራጣት በትንሹ አንጀት ሲታሰር “ከእንግዲህ እነዚህ ወንድማማቾች ለማጣላት፣ ጸብ ለመጫር፣ ሰላም ለመንሳት የሚንቀሳቀስ አካል ያለ እንደሆነ እድሜው ጤናውን ይታሰር” በማለት የአንድነት ሰንሰለቱ እያጠናከሩ ይሄዳሉ።

የሀገር ሽማግሌዎች ታርዶ ሆዱ የተቀደደው ፍየል ይዘው ወደ ዛፍ ስር ይወሰዳሉ። እዛ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ስራ ይሰራል። ያውም ጉድጓድ መቆፈር ነው። በተቆፈረው ጉድጓድ የፍየሉን ሆድ እቃና ሆዱን የተቀደደበት ቢላ ይቀበራል። ይህንን ድርጊት ሲፈጽሙ “በመካከላችን የተፈጠረው ሰላም ያደፈረሰ፣ የጣሰ፣ ጉዳ ያፈረሰ ያለእድሜው ይቀበር” ተብለው በጋራ አፈሩ ወደ ጉድጓዱ ይመልሱታል።

የቀረው የፍየሉ አካል አውሬ እንዲበላው ይጣላል። ጸብ አጫሪው “እነዚህ ወገኖች ለማባላት የሚንቀሳቀስ ያለ እንደሆነ እድሜው ይጠር፣ አውሬ ይብላው ብለው አንድነታቸው በጉዳ ገምደው አሰሩት።

የእነዚህ ወገኖች የጉዳ ስነስርዓት ከድንበርተኛ ጋር የሚፈጸም ስነ ስርዓት ልዩነት እንዳለው ማጤን ያስፈልጋል።

ደንበርተኞች ጉዳ ሲያያዙ ድንበር አይጋፉም፣ በትዳር አይተሳሰሩም። ስርዓቱ ለዘላለም የጸና ይሆናል። ያም ማለት አባት ለልጅ ፣ ልጅ ወደ ልጅ እያለ በንግርት ይተላለፋል። የመስቃን እና ማረቆ ወንድማማቾች ጉዳይ ግን ጠላትን መፍጠር እንጂ ትዳር መመስረትን አይከለክልም።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የእርቅ ስነስርዓት በተፈጸመበት ወቅት ሠላም በስምምነት፣ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በመተሳሰብ እና በመከባበር የመኖር ውጤት እንደሆነ አብራርተዋል።

የሰው ልጅ አብሮ ከሚኖረው ሰው እንዲሁም ከፍጥረታት ጋር ሰላማዊ መስተጋብር እንዲኖረው የሁላችንም ኃይማኖት አጥብቆ ያስተምራል፡፡ ሰው እራሱን በጎሳ፣ በዘር፣ በአካባቢ፣ በኃይማኖት እና በፖለቲካ ሳይከፋፍል ከሰው ልጅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእንስሳትም ጋር ቢሆን በሰላም የመኖር ልምድን አዳብሮ ጠንካራ የሰላም እሴቶችን ገንብቶ ቆሻሻና ከፋፋይ ነገሮችን ጠቅልለው ለሚያያጎርሱን ኃይሎች እጅ ሳንሰጥ ሰላማችንን ልናስጠብቅ ይገባል፡፡

ብዙ ጊዜ በሰዎች መካከል ሰላም እንዲጠፋ የሚያደርጉ ነገሮች የራስን ጥቅም ብቻ ለመጠበቅ በሚደረግ ትግል ነው፡፡ ስለሆነም ለአንተ እንዲሆንልህ የምትፈልገውን ለሌላው አድርግ፣ በአንተ እንዲሆንብህ የማትፈልገውን በሌላው አታድርግ።
ሰላም ለሀገራችን ሰላም ለህዝባችን እንዲሆን ከልብ እንመኛለን!!

               ጥር 30/2014 ዓ.ም

የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *