የግብርና እድገት ፕሮግራም (AGP) አዳዲስ እና የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች በማቅረብ ምርትና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው በቸሃ ወረዳ በመስኖ ልማት የተደራጁ አርሶ አደሮች ገለጹ።

መበወረዳው የግብርና እድገት ፕሮግራም የምዕራፍ ሁለት ማጠናቀቂያ መርሀግብር በእምድብር ከተማ ተካሔደ።

በወረዳው በግብርና እድገት ፕሮግራም ተጠቃሚ ከሆኑ አርሶ አደሮች መካከል ወጣት ዳንኤል ሺፈታ ይገኝበታል ። ወጣት ዳንኤል ሺፈታ በ2006 ዓም የግብርና እድገት ፕሮግራም ባደረገለት የጄኔሬተር፣ የምርጥ ዘርና የኬሚካል ድጋፍ በሁለት ሄክታር መሬት ነበር የመስኖ ስራውን የጀመረው።

አሁን የማምረት አቅሙን በማሳደግ 25 ሄክታር መሬት ተረክቦ የተለያዩ የመስኖ ስራዎች በማከናወን አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል ።

እንደ ወጣት ዳንኤል ገለፃ የግብርና እድገት ፕሮግራም ( AGP) ምርታማነታቸውን የተረጋገጡ ዘሮች እና የአፈር ማዳበሪያ ማቅረቡ በገበያ ላይ የሚስተዋለው የግብርና ውጤቶች አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ወይዘሮ ማይሙና ሙደሲር እና አቶ ፉአድ ከድር በወረዳው በመስኖ ልማት በመሰማራት ውጤታማ አርሶአደሮች ሲሆኑ የግብርና እድገት ፕሮግራም ከሚያቀርባቸው ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ሸራና ጀነሬተር በተጨማሪ በየደረጃው የሚገኙ የወረዳው አስተዳዳሪ ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያደርጉላቸው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ዘርፍ አዋጭና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የላቀ በመሆኑ ሌሎች ወጣቶች፣ ሴቶችና አርሶአደሮች በግብርና ስራ በመሰማራት ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የቸሃ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምንሳ በምዕራፍ ሁለት የፕሮግራሙ ማጠቃለያ ወቅት እንደተናገሩት በ2ኛው የግብርና እድገት ፕሮግራም በሰብል ልማት፣ በእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ የተሰሩ ስራዎች አበረታች ነበሩ።

ባለፉት አምስት አመታት በወረዳው የመስኖ ልማት ስራ ውጤታማ ለማድረግ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል ብለዋል።

በመሆኑም በወረዳው በ2003 ዓ.ም በመስኖ ይለማ ከነበረው 178 ሄክታር መሬት በ2ኛው ዙር መጨረሻ ወደ 3ሺህ 500 ሄክታር ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በሶስተኛው ዙር የግብርና እድገት ፕሮግራም የወረዳው አርሶአደሮች በምግብ እራስን ከመቻል ባለፈ ገበያ ላይ የሚስተዋለው የአቅርቦት እጥረት ችግር መቅረፍ እንዲችሉ ይሰራል ብለዋል።

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ይልማ በበኩላቸው በወረዳው የተደራጁ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች አርሶአደሮች ተጠቃሚነታቸውን ለማሳዳግ የግብርና እድገት ፕሮግራም የተዳቀሉ ምርጥ ዘሮች፣ የውሃ ፓምፕና ኬሚካሎች እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።

ፕሮግራሙ አርሶ አደሮች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የግብርና ምርቶች በማምረት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ አልሞ እየሰራ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል።

የግብርና እድገት ፕሮግራም (AGP) መንግስት በመደበኛ በጀት አቅዶ በማይሰራባቸው የመስኖ መሰረተ ዝርጋታዎች፣ የድልድይ፣ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል፣ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል በመገንባት አበረታች ተግባራት ማከናወኑን አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል።

የቸሃ ወረዳ የግብርና እድገት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ትግስቱ ናንሳነ እንደተናገሩት የወረዳው አርሶአደሮች በሰብል ልማትና በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ያላቸውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ፕሮግራሙ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

እንደ አስተባባሪው ገለፃ በሁለት ምዕራፎች የአርሶአደሮች ማሰልጠኛ ማዕከላት በቁሳቁስ በማሟላት አርሶአደሮች ልምድ የሚቀስሙበት ማዕከል ማድረግ ተችሏል።

አርሶአደሮች ዝርያቸው የተሻሻለ ከብቶች በማርባት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጤና ኬላዎች በሰው ኃይልና በቁሳቁስ እንዲሟሉ ማድረግ መቻሉን አቶ ትግስቱ ገልጸዋል።

ምርታማነታቸውን የተረጋገጠ 4 ሚሊዮን የቡና ችግኞች በማፍላት ለአርሶአደሮች ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከአንድ ሺህ በላይ የተከተቡ የአቮካዶ ችግኞች ማሰራጨት መቻሉን አስተባባሪው ጠቁመዋል ።

ፕሮግራሙ አርሶአደሮች የሚያመርቷቸው ምርቶች ሳይበላሹ ወደ ገበያ በቀላሉ ለማቅረብ የድልድይ ግንባታ የተከናወነ ሲሆን ለህብረት ማህበራት አራት መጋዘኖች፣ የግብይት ማዕከላት ማስገንባት ችሏል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *