የጉራጌ የመስቀል በዓል አከባበር የአደባባይ ፌስቲቫል ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

መስከረም 15/2015

የጉራጌ የመስቀል በዓል አከባበር የአደባባይ ፌስቲቫል ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የዘንድሮ የመስቀል በዓል በወልቂጤ ማረሚያ ተቋም በህግ ጥላ ስር ከሚገኙ ታራሚዎች ጋር በድምቀት ተከበረ።

በጉራጌ ብሔር ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የመስቀል በአል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።

ይህንን ታላቅ በዓል ከቤት አልፎ የአደባባይ ፌስቲቫል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ገልጸዋል።

የመስቀል በዓል በማይዳሰስ የአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ የጉራጌ መስቀል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

የመስቀል በዓል በድምቀት ለማክበር ከነሐሴ 12 ጀምሮ ዝግጅት የሚደረግ ሲሆን ሁሉም የቤተሰብ አባላት የራሳቸው የስራ ድርሻ በመውሰድ ሚናቸው በብቃት ይወጣሉ።

በዓሉ በቤተሰብ እና በአካባቢ ደረጃ በድምቀት የማክበር ስነ -ስርዓቱ እንደተጠበቀ ለአቅመ ደካሞችና ጧሪ ለሌላቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በጋራ ማክበር ይገባል ብለዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ የመስቀል በዓል የተጣሉ ወገኖች የሚታረቁበት፣ የተቸገሩ የሚረዱበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ በአካባቢ ልማት የሚወያዩበት ነው ብለዋል።

መስቀል በጉራጌ ከኢትዮጵያውያን ባለፈ የውጭ ሀገር ዜጎች በዓሉን መታደማቸው የጎብኚዎች ቁጥር የሚያሳድግ በመሆኑ የአደባባይ ለፌስቲቫል ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አቶ መሀመድ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ገ/መድህን በበኩላቸው የመስቀል በዓል ከኃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በድምቀት ለማክበር ይሰራል ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር የመረዳዳት፣ የመከባበር እና የአብሮነት እሴቶቻችን ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

የ2015 ዓ.ም የመስቀል በዓል ከወትሮ በተለየ መልኩ በወልቂጤ ማረሚያ ተቋም በህግ ጥላ ስር ከሚገኙ ወገኖች ጋር ማክበሩ በዓሉ ይበልጥ እንዲደምቅ እንዳደረገው አቶ ተመስገን ገልጸዋል።

የወልቂጤ ማረሚያ ተቋም አዛዥ ኢንስፔክተር ሚስባ ግራኝ በበኩላቸዉ በተቋሙ 683 የህግ ታራሚዎች የሚገኙ ሲሆን ለታራሚዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው ከማድረግ በተጨማሪ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው ለማሟላት የቀለም ትምህርት፣ የሙያ ስልጠና፣ የንቃተ ህግ ትምህርትና የምክር አገልግሎት በመስጠት በልማት ስራ በንቃት እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተቋሙ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች የመስቀል በዓል በተቋሙ መከበሩ ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል።

የእርምት ጊዜያቸው አጠናቀው ከህብረተሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ቀደም ሲል የበደሉትን ማህበረሰብ በመልካም ስራ ለመካስ እንደሚሰሩ ቃልም ገብተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *