የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ በግል ጤና ተቋማት ተግባር አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ከተቋማቶቹ ጋር በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት በመንግስት የጤና ተቋማት የማይሸፈኑ አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ በመስጠት የግል ጤና ተቋማት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጥሩ አግልግሎት የሚሰጡ የተወሰኑ የግል የጤና ተቋማት መኖራቸውን በማከል፡፡

በግል ጤና ተቋማት የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል፡፡

በአንዳንድ የግል ጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች በጤና ስታንዳርድ መሰረት ያለመሆኑ፣ ህብረተሰቡ በቋንቋው አገልግሎት ያለማግኘት፣ ህጋዊ አሰራር ተከትለው በማይሰሩ ተቋማት ላይ እርምጃ በሚወሰድበት ጊዜ ተግባራዊ እንዳይደረግ ጫና የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ኃላፊው አስገንዝበዋል፡፡

የጤና ስራ ትርፍን ብቻ መሰረት ተደርጎ የሚሰራ ሳይሆን ከሰው ህይወት ጋር የሚገናኝ በጥንቃቄ የሚሰራበት የአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን የገለጹት አቶ አየለ በግል የጤና ተቋማት ያለ ሀኪም ትዕዛዝ መድሃኒት የሚሸጡና ለአንድ በሽታ ተገቢ ያልሆኑ በርካታ መድሃኒቶችን የሚያዙ መኖራቸውን በሱፐር ቪዥን የተረጋገጠ ስለሆነ በቀጣይ ችግሮቹ ለማረም ይሰራል፡፡

በቀጣይ የዞኑ ጤና መምሪያ ከግል የጤና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀና ፍትሃዊ ለማድረግና ደረጃቸውንም እንዲያሻሽሉ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አየለ ገልጸዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብዓት ጥራት ቁጥጥር የስራ ሂደት አስተባባሪ ወ/ሪት ዘይነባ ጀማል በበኩላቸው በቀጣይ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ችግር ያለባቸው ተቋማት በመለየት ግንዛቤ በመፍጠር የማብቃት ስራ እንደሚሰራና ይህንን ተከትለው ለውጥ በማያመጡት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል፡፡

የግል ጤና ተቋማት ሳምንታዊ ሪፖርት ለሚመለከተው አካል የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የገለጹት ወ/ሪት ዘይነባ በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ የዶላር ምንዛሪ ጨምሯል በሚል ሰበብ በህክምና አገልግሎትና በመድሃኒት ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ተቋማት አስፈላጊውን ማስተካከያ በማድረግ የመድሃኒት መሸጫ ዋጋ በዝርዝር በየተቋማቱ እንዲለጥፉ አስገንዝበዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት መምሪያው ከግል የጤና ተቋማት ጋር ውይይት ማካሄዱ በአገልግሎት አሰጣጣቸው ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመቅረፍ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው መሰል መድረክ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ የግል ጤና ተቋማት ተግባር አፈጻጸምና የድጋፍና ክትትል ግብረ-መልስ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸው በቂ ግንዛቤ ከተያዘ በኋላ የቀጣይ አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *