የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳቹ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

መስከረም 14/2015 ዓ.ም
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳቹ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዋና አስተዳዳሪ በመልዕክታቸው የመስቀል በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ አኗኗርና ወግ በተላበሰ መልኩ የሚከበር ቢሆንም የበዓሉ አከባበር ደረጃና የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡

በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ እጅግ በደመቀ፣ በልዩ ጥበብና በተለየ ስሜት ከሚከበሩና በርካታ የብሄረሰቡ ባህላዊ እሴቶች መገለጫ ከሆኑ ዋና ዋና ሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት መካከል አንደኛው በወርሃ መስከረም አጋማሽ ላይ የሚከበረው የጉራጌ መስቀል በአል አንዱ ነው ብለዋል።

ለጉራጌ ብሄረሰብ የመስቀል በአል የተጣላ የሚታረቅበት፣ ተራርቆ የሚኖሩ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ የሚገናኝበት፣ ታላላቆች የሚከበሩበት፣ አንድነት የሚደምቅበትና ፍቅር የሚሞቅበት በዓል ነው።

ለወራት ተደክሞበት ለወር የሚደሰቱበት፣ በስራውም በደስታውም ሁሉንም የብሄረሰቡ አባላት በንቃት የሚሳተፉበት፣ እድሜና ፆታ ሳይለይ የሁሉም መብትና ፍላጎት እኩል የሚከበርበት፣ እንኳንስ የሰው ልጅ የቤት እንስሳትም የሚጠግቡበትና የሚደሰቱበት፣ ፍቅር የሚደራበትና አብሮነት የሚደምቅበት ልዩ በዓል ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራችን በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን አነሳሽነት ሀገር ለማዳን ጦርነት ውስጥ ብትሆንም የህልውና ጦርነቱ በድል እስኪጠናቀቅ የዞኑ ህዝብ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

የኢትዮዽያ እውነትና ሀቅ ገሀድ ወጥቶ የሰላምና የልማት ምድር እንድትሆን፣ ልጆቿ በስደት የሚሸሽዋት ሳይሆን ሌሎች ሰላምንና ፍቅርን ፈልገው የሚጠጉባት የበለፀገች አገር እንድትሆን ምዕመኑ አጥብቆ እንዲጸልይ ጠይቀዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በዞናችን የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በዓሉን ሲያከብሩ ከተቸገሩ ወገኖችና በየአካባቢው የሀገራችን ዳር ድንበር ለማስከበር ከዘመቱ ወጣቶች ቤተሰብ ጋር በአብሮነት በማክበር ረገድ የነበረዉ ባህል ከምንጊዜዉም በላይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችና ለሁሉም የዞናችን ህዝቦች በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላምና በጤና አደረሳቹ ብለዋል።
።።።።።።።።።።መልካም በዓል ።።።።።።።።

እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *