የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለመላዉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳቹ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዋና አስተዳዳሪ በመልዕክታቸው የመስቀል በዓል አጀማመር መሰረት የሆነው የእየሱስ ክርስቶስ መስቀል መገኘት ጋር የተያይዘ ሲሆን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማለትም ከንግስት እሌኒ አገዛዝ ዘመን ጀምሮ እንደሚከበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ ብለዋል፡፡

ይህ ታላቅ በዓል በሁሉም የኢትዩጵያ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ አኗኗርና ወግ በተላበሰ መልኩ የሚከበር ቢሆንም የበዓሉ አከባበር ደረጃና የሚሰጠው ትኩረት ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡

በጉራጌ ብሔረሰብ ዘንድ እጅግ በደመቀ፣ በልዩ ጥበብና በተለየ ስሜት ከሚከበሩና በርካታ የብሄረሰቡ ባህላዊ እሴቶች መገለጫ ከሆኑ ዋና ዋና ሀይማኖታዊና ባህላዊ በአላት መካከል አንደኛውና ግንባር ቀደሙ በወረሀ መስከረም አጋማሽ ላይ የሚከበረው የጉራጌ መስቀል በአል አንዱ ነው ብለዋል።

ለጉራጌ ብሄረሰብ የመስቀል በአል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያየ የሚገናኝበት፣ ታላላቆች የሚከበሩበት፣ አንድነት የሚደምቅበትና ፍቅር የሚሞቅበት በአል ነው።

ለወራት ተደክሞበት ለወር የሚደሰቱበት፣ በስራውም በደስታውም ሁሉንም የብሄረሰቡ አባላት በንቃት የሚሳተፉበት፣ እድሜና ፆታ ሳይለይ የሁሉም መብትና ፍላጎት እኩል የሚከበርበት፣ እንኳንስ የሰው ልጅ የቤት እንስሳትም የሚጠግቡበትና የሚደሰቱበት፣ ፍቅር የሚደራበትና አብሮነት የሚደምቅበት ልዩ በአል ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የመስቀል በአል ከሀይማኖታዊ አስተምህሮቱ እና ከመንፈሳዊ እውነትነቱም እንዲሁም ድንቅና ውብ ከሆኑ ባህላዊ እሴቶችና ክዋኔዎች ባሻገር የሚያስተምረን እና በውል እንድናስተውል የሚያስገድደን አንድ ቁም ነገር አለ፡፡

እሱም እውነት የቱንም ያክል ዓመታት፣ በምንም ያክል የውሸትና ቅጥፈት ብትሸፈንም በዘላቂነት ልትቀበር እንደማትችል ነው ለዚህም ማሳያ ጌታችን መዳኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል እውነታ ከብዙ ዘመናትና ልፋት በኋላ ከተቀበረበት መገኘቱ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ሀገራችን በውስጥ ባንዳዎችና በውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በበርካታ ችግሮች ውስጥ መሆንዋ ገልፀው ነገር ግን እውነትና ሀቅዋ ገሀድ ወጥቶ የሰላምና የልማት ምድር፣ ልጆቿ በስደት የሚሸሽዋት ሳይሆን ሌሎች ሰላምንና ፍቅርን ፈልገው የሚጠጉባት የበለፀገች አገር እንድትሆን ምዕመኑ አጥብቆ እንዲፀልይ ጠይቀዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በዞናችን የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ በአሉን ሲያከብሩ ከተቸገሩ ወገኖችና በየአካባቢው የሀገራችን ዳር ድንበር ለማስከበር ከዘመቱ ወጣቶች ቤተሰብ ጋር በአብሮነት በማክበር ረገድ የነበረዉ ባህል ከምንጊዜዉም በላይ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

በመጨረሻም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችና ለሁለም የዞናችን ህዝቦች በድጋሚ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላምና በጤና አደረሳቹ ብለው ህዝበ ክርስትያኑ ይህንን በአሉን ሲያከብር ማህበራዊ ዕርቀትን መጠበቅና ሌሎች መሰረታዊ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ በመተግበር እና የአካባቢው ሰላም በመጠበቅ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *