የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል ለመላው የዞኑ ህዝብና ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ2014 ዓመተ ምህረት አዲስ አመት በሰላም አደረሳቹ ሲሉ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

አዲስ አመት በሰው ልጆች ዘንድ በርካታ አዲስ ተስፋ፣ምኞት፣እቅድ እና አስተሳሰብ ይዞ ይመጣል።

በመሆኑም በአዲሱ አመት በአንድ በኩል ባለፈው አመት የነበሩ መልካም ስራዎችና ያስመዘገብናቸው ትላልቅ ድሎች የበለጠ አጠናክረን የምናስቀጥልበት፣እንዲሁም አዳዲስ ሀሳቦችና እቅዶች አቅደን የምንተገብርበት በሌላ በኩል እዚህም እዚያም የነበሩ ውስንነቶችና ያልተገቡ ድርጊቶች ከልብ ተፀፅተን በይቅር ባይነት በመሻገር በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመቻቻልና አንድነታችንን በማጠናከር የምንክስበት አመት መሆን አለበት ብለዋል።

ያሳለፍነው አመት ሀገራችን በመላው ህዝብ ተሳትፎ በርካታ ድልና ውጤት ያስመዘገበችበት፣በርካታ እድገትና ብልፀግናችን የማይመቻቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን አንገት ያስደፋንበት አመት እንደነበረ ገልፀው እነዚህ በርካታ ድሎቻችንና የብልፀግና ጉዞ ያልተመቻቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን በተለይም የህዋሀት አሸባሪው ቡድንና ተባባሪዎቹ በፈጠሩብን ጫናና ትንኮሳ በርካታ ዋጋ የተከፈለበት አመትም ነበር ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዉጭና ከዉስጥ የተቃጣባት ጥቃት ለመመከትና ከጠላት ለመከላከል እንዲሁም አባቶቻችን ከነ ሙሉ ክብሯ ያስረከቡን ታላቅ ሀገር ላለማስደፈር ህይወታቸዉን እየሰጡ ያሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የዞናችን ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ገልፀው በቀጣይም ህዝባችን የሀገራችን ሰላም እስኪረጋገጥ ከመላዉ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ከመቼዉም ጊዜ በላይ ከጎናቸዉ መቆም እንደሚገባም ገልፀዋል።

2013 አመተ ምህረት ህዝቡ አንድነቱ ያጠናከረበት፣ትላልቅ ስራዎችና ሁነቶች የተከናወኑበት እንዲሁም በዞናችን ህዝቦች ትብብር የበጎ ፍቃድ ስራዎች በተጠናከረ ሁኔታ የተከናወኑበትና የበርካታ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን መደገፍና ማገዝ የተቻለበት አመት እንደነበረ ገልፀው ይህ አንድነትና መረዳዳት በአዲሱ አመትም ተጠናክሮ የሚቀጥልበት መሆን አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ያለ ምልአተ ህዝቡ ልባዊ ድጋፍና ንቁ ተሳትፎ በሀገራችንም ሆነ በዞናችን አስተማማኝ ሰላም፤ ልማትና ዴሞክራሲ እዉን ማድረግ ከቶዉንም አይቻልም፡፡

በመሆኑም ሁላችንም በሀገራችንም ሆነ በዞናችን የተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ፣ የታለመውን የሀገራችንና የዜጎቻችን ብልፅግና እንዲያመጣ ከመንግስት ጎን በመቆም ያልተቆጠበ ድጋፍና ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረን በዚህ አጋጣሚ ጥርዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

አዲሱን አመት የሀገራችን ጠላት የሆነዉን ጁንታ ሙሉ ለሙሉ ግብአተ መሬት ፈጽመን በተድላና በደስታ፣በሰላምና በጤና፣በመቻቻልና በመረዳዳት የምናሳልፍበት ይሆን ዘንድ መልካም ምኞታቸው ገልፀዋል።

አዲሱ አመት የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያየ የሚገናኝበት፣ ታላላቆች የሚከበሩበት፣ አንድነት የሚደምቅበትና ፍቅር የሚሞቅበት እንዲሁም ከጥቃቅን አስተሳሰቦችና አጀንዳዎች ተላቀን ሁላችንም የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥረን እጅ ለእጅ ተያይዘን ሀገራችንና ዞናችን ወደ እድገት ማማ ማሻገር የሚችሉ የአስተሳሰብ ከፍታ በማምጣት ትልልቅ ተግባራት የምንፈፅምበት አመት እንዲሆን ጠይቀዋል።

በመጨረሻም አቶ መሀመድ በአሉ ስናከብር የተቸገሩና አቅመ ደካሞች በመርዳት፣እየጨመረ የመጣው የኮሮና ወረርሽኝ ሳንዘነጋ እየተጠነቀቅንና እንዲሁም የአካባቢያችን ሰላም እየጠበቅን እንዲሆን በማሳሰብ በድጋሚ መልካም አዲስ አመት መልካም በአል እንዲሆን ተመኝተዋል።

               መልካም አዲስ አመት!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *