የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ለ1 ሺህ 4 መቶ 45ኛ ዓመተ ሂጅራ የሚከበረዉን የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል አስመልክተዉ ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳቹሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የአረፋ በአል ሲያከብር የተቸገሩትንና አቅመ ደካሞችን በመርዳትና የአብሮነት ባህሉን ከመቼዉም ጊዜ በላይ ማጠናከር ይኖርበታል።

ሀይማኖታዊ በዓላት እሴቶችን በማጎልበት፣ በተገቢዉ በማልማትና በመጠበቅ ለቀጣይ ትዉልድ ማስተላለፍ ይገባልም ብለዋል።

የአረፋ በአል በዞኑ ማህበረሰብ ዘንድ በተለየ መልኩ በድምቀት የሚከበር እንደሆነም ጠቁመዉ ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን አደረሳቹሁ ብለዋል።

የአረፋ በአል የመረዳዳት ፣ የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴቶች እንዲጎለብቱ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር የተቸገሩትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት በደስታ ማሳለፍ እንዳለባቸዉም ተናግረዋል።

የአረፋ በአል የአብሮነት፣ የአንድነትና የመቻቻልን እሴት መሰረት እንደሆነም የተናገሩት አቶ ላጫ በዞኑ ህዝቦች ዘንድ እጅግ በደመቀ፣ በልዩ ጥበብና በተለየ ስሜት የሚያከብሩት በአል ሲሆን የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተለያየ የሚገናኙበት፣ ታላላቆች የሚከበሩበት፣ አንድነት የሚደምቅበት ነዉ ብለዋል።

በዓሉ ከሀይማኖታዊ ፋይዳ በተጨማሪ ባህላዊ ይዘትም አለዉ ያሉት አስተዳዳሪዉ በሀገሪቱ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተዉ የነበሩ የብሔሩ ተወላጆች ወደ ትዉልድ አካባቢያቸዉ በመምጣት ከቤተሰብ ፣ ከጓደኞቻቸው ከዘመድ አዝማድ ጋር በመሆን በዓሉ በደስታ የሚያከብሩበትና በአካባቢ ጉዳዮች ላይና ችግሮች ላይ በስፋት የሚመክሩበት በዓልም እንደሆነም ተናግረዋል።

የዒድ አል-አድሓ /አረፋ/ አከባበር አባት ልጃቸውን ለአላህ ለመሰዋት ያደረጉት ቁርጠኝነት የተመላበት ውሳኔ እና ለመስዋዕትነት የቀረበው ልጅም ያሳየው የተለየ ጽናት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን በዓሉ እንዲከበር ትልቁ ምክንያት የሆነው የፍፁም ታዛዥነትን ተከትሎ ከአምላክ የተቸረ የፍቅርና የስጦታ በዓል እንደሆነ ሁሉ የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር በእውነት ለቆመለት ዓላማ በቅንነት ከታዘዘ መልካም ነገሮችን ማግኘት እንደሚችል በግልፅ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ለሀይማኖቱ አስተምህሮት ፍፁም ታዛዥ በመሆን በህዝብ ውስጥ ጥላቻን ቂም-በቀልን መለያየትን መነቋቆርን ለሚሰብኩ የተዛባ መረጃ በማቀበል ለዘመናት በፍቅር በመተሳሰብ አብሮ በኖሩ ህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር በማህበራዊ ሚድያና ባገኙት አማራጭ ሁሉ እየተጉ ላሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ድል መንሳትና እኩይ አላማቸውን ማምከን የሁሉም ሰዉ ሀላፊነት መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

የአረፋ በዓል የይቅር ባይነትና የፍቅር መታሰቢያ ተምሳሌትም እንደሆነ ተናግረዉ አባታችን አደም እና እናታችን ሀዋ የፈጣሪን ትዕዛዝ በመጣስ ከጀነት ወደ ምድር ሲወረወሩ የተለያየ ቦታ በመውደቃቸው ተለያይተው ከቆዩ በኋላ በአላህ እዝነትና ይቅር ባይነት አረፋ ላይ ተገናኝተዋል።

የአረፋ በዓል ሁሉም ኢትዮጵያዉያን በጋራ የሚያከብሩት እንደሆነና በእምነት ሳይለዩ በጋራ በመሆን በፍቅር በመተሳሰብ የሚያከብሩት በዓልም እንደሆነም ነዉ ያነሱት።

በዞኑ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም አመላክተዉ ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 4 መቶ 45ኛ የኢድ አል አድሃ የአረፋ በአል በሰላም አደረሳቹሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *