የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለመላዉ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።


ለ1445ኛ አመተ ሒጅራ ኢድ አል-አደሃ አረፋ በዓልን በማስመልከት የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የመልካም ምኞት መግለጫ—

የአረፋ በዓል ከተቸገሩ ወገኖች አብሮ በማሳለፍ ፣ በመረዳዳት በደስታ ልናሳልፈዉ ይገባል።

በጉራጌ ዞን ውስጥ የምትኖሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ምዕመንና ምዕመናት እንዲሁም በሀገራችን ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ የምትኖሩ ብሎም ከሀገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በሙሉ በእስልምናችን አስተምሮት መሰረት ለ1445 አመተ ሒጅራ በድምቀት ለሚከበረው ኢድ አል-አደሃ አረፋ በዓል እንኳን በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!

በዲናችን (በእስልምና) አስተምህሮት በግልጽ እንደተቀመጠው በዙል ሂጃህ ወር በ9ኛ ቀን የሚከናወነው የአረፋ ሥርዓት የእስልምና ሃይማኖት የመጨረሻ ከፍታውን ያገኘበት እና የቁርአን የመጨረሻ አንቀፆች ለነቢዩ መሀመድ (የአላህ ሰላምና እዝነት በእርሳቸው ላይ ይሁንና) የወረደበት እለት ከመሆኑም በተጨማሪ በአንድ በኩል አባታችን ነብዩላህ አደምና እናታችን ሀዋ ከጀነት ከወጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር የተገናኙበትና “አወቅኩሽ?” “አወቅኩህ?” የተባባሉበትን ድንቅ ተዓምራት ማስታወሻም ጭምር ነው፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ነቢዩላህ ኢብራሂም (የአላህ ሰላም በእሳቸው ላይ ይሁንና) በአምላካችን አላህ ትዕዛዝ አንድያ የበኩር ልጃቸውን ነብዩላህ ኢስማኢልን ለመስዋዕት አቅርበው ለፈጣሪያቸው ትዕዛዝ ከመገዛታቸው የተነሳ በልጃቸው ምትክ የበግ መስዋዕትነት ከሰማየ ሰማያት የተተካላቸው መሆኑን የምናስታውስበት ዕለት በመሆኑ ለሁላችንም የታዛዥነትን ከፍታ እና የእምነትን ልዕልና የሚያጎናፅፍ ግሩም መንፈሳዊ በዓል ነው፡፡

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ከእስልምና ማዕዘናት መካከል አንዱ የሆነው የሐጅ ስነ-ስርዓት የሚከወንበት ሲሆን በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ በዋናነት ከምንቀስማቸው ትምህርቶች መካከል አንድነትን፣ እኩልነትን፣ ታጋሽነትን፣ ታዣዥነትን፣ መስዋትነትን፣ በአላህ ላይ መወከልን ፣ መተሳሰብን እና አለምአቀፍ ወንድማማችነትን ነው፡፡

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንና ምዕመናት ለአንድ አላማ፣ በአንድ ቦታ፣ በአንድ አይነት አለባበስ፣ በአንድ አይነት የአምልኮ ተግባር የሚሰባሰቡበት ፤ ዘረኝነት እና ቁሳዊ መበላለጥ በእስልምና ቦታ የሌለው መሆኑን በተግባር የሚገለፅበት ስነ-ስርዓት ነው፡፡

የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የሰው ልጆች እንደ ማበጠሪያ ጥርስ እኩል መሆናቸውን በዘር፣በቀለም፣በብሄር እና በውጫዊ መገለጫዎች የማይበላለጡ መሆኑን በተግባር የምንማርበት፣ እኩልነትን ብቻ ሳይሆን በዓሉ የሁሉም የደስታ ቀን መሆን ስለሚገባው በኡዱሂያ እርድም ከሚታረደው እርድ አንድ ሶስተኛውን ለሚስኪኖች እና ለአቅመ ደካሞች እንድንለግስ፣ማህበራዊ ትስስራችን ይበልጥ ይጠናክር ዘንድም ሌላውን አንድ ሶስተኛ ለጎረቤቶቻችን፣ለዘመድ አዝማድ እና ለሌሎች እንድናካፍል የታዘዝንበት ድንቅ የአንድነት እና የመተሳሰብ በዓል ነው፡፡

የኛ የሙስሊሞች ጉዳይ በአምልኮ ጉዳይ ብቻ ያልተገደበና የሀገራችን ሁለንተናዊ ጉዞን የሚመለከት መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። የኛ ሚና በሁሉም ሀገራዊ ጉዳዮችና እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ በሚመለከቱ የሰላም፣ የእድገት፣ የለውጥ ጉዞ ሁሉ የተባበረ ተሳትፎ ማድረግን የሚሻ ነው። በመሆኑም በተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ሳይገድቡን ከመንግስት ጋር እኩል የምንጋራውና ተባብረን የምናሳካው የጋራ ሀገራዊ ጉዳይ ነው ፡፡ በመሆኑም ለሀገራችን ሰላምና እድገት በዱዓ የተመኘነውን በተግባር እውን ሆኖ እንድናየው ያልተቋረጠ ርብርብ የማይናቅ ውጤት ስለሚያስመዘገብ የጀመርነውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክረን በመቀጠል በውጤት እንድናስመሰከር ልናስታውስ እንወዳለን፡፡

በስተመጨረሻም አላህ (ሱ.ወ.) ኢትዮጵያ አገራችንን እና ወገኖቻችንን ሰላም እንዲያደርግልን እየለመንን በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖቻችንን ከማሰብ ባሻገር ያለንን ተካፍለን የዒድ ደስታችን አጋር እንድናደርጋቸው በዞኑ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ስም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የጉራጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት
ወልቂጤ ሰኔ 08/2016
ኢድ ሙባረክ ተቀበለላሁ ሚና ወ ሚንኩም ሷሊሀል አዕማል !!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *