የጉራጌ ዞን አስተዳዳር ለዞኑ ህዝቦች እና ለመላው ኢትዮጵያዉያን እንኳን ለ2017 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ እያለ መልካም ምኞቱ ይገልፃል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በተጠናቀቀው በጀት አመት በሀገራችን በተለይም በዞናችን ህብረተሰባችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በግብርና ፣ በትምህርት፣ በጤና በመንገድና በጸጥታው ዘርፎች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች እንደነበሩ አቶ ላጫ በመግለጫቸው አሳውቀዋል።

በተለይም የትምህርት ውጤት ስብራት ለመጠገንና የትምህርት ተቋማት ደረጃ ለማሳደግ የዞኑ ማህበረሰብ ያደረገው ተሳትፎ እጅግ የሚያስመሰግን እንደነበረ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ተጀምረው ግንባታቸው የተጓተቱ የአዳሪ ትምህርት ቤት፣ የዞኑ አስተዳደር ህንፃ ግንባታ፣ የጉራጌ የባህል አዳራሽ ህንፃዎች የግንባታ ደረጃቸው ለማፋጠን በተወሰደው ቆራጥ እርምጃ አፈጻፀማቸው የሚበረታታ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በዞኑ ለተመዘገቡ ለውጦች አመራሩ፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ ባለሀብቶች እና መላው ህዝባችን ያሳየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ እንደነበር አቶ ላጫ ገልፀዋል።

በመሆኑም የምንቀበለው አዲስ አመት ሁሉም አዲስ መንፈስ ተላብሶ የጀመርናቸው የልማት ስራዎች ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዞናችን በተለያዩ አካባቢዎች የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናቀው ህዝባችን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ወቅቱ የቴክኖሎጂ እውቀት፣ የፈጠራ ችሎታና ታታሪን የሚጠይቅበት በመሆኑ ተማሪዎች በበዓላት ሳይዘናጉ በትምህርት ገበታቸው ተገኝተው በመማር የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ከወዲሁ ተግተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አዲሱን አመት ስንቀበል መንፈሳችን አድሰን፣ ጠንካራ የስራ ወኔ ሰንቀን ባለፈው አመት የነበሩብንን ድክመቶች አርመን ለተሻለ ለውጥ መነሳሳት አለብን ብለዋል።

ዘመኑ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመከባበር እና ህብራዊነት የሚያብብበት ይሁንልን።
መልካም አዲስ ዓመት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *