የጉራጌ ዞን አስተዳደር የ2017 በጀት አመት የአንደኛው ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም የዞኑ መስተዳደር ምክር ቤት አባላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገመገመ።


የጉራጌ ዞን አስተዳደር የ2017 በጀት አመት የአንደኛው ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም የዞኑ መስተዳደር ምክር ቤት አባላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገመገመ።

የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የተቋቋሙት የሰንበት ገበያዎች ውጤታማ ለማድረግ በቂ የግብዓት አቅርቦት መኖር እንዳለበት የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ንግድና ገበያ ልማት፣ የግብርና መዋቅር እና የህብረት ስራ ማህበራት በቅንጅት ሰርተው ሸማቹ ከአምራች ጋር ማገናኘት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በግብርና በኩታ ገጠም ማሳዎች በተለይ የበቆሎ እና የጤፍ እንዲሁም በሌሎች ሰብሎች ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል ይኖርበታል ።

ከዚህ በፊት ያልታረሱ መሬቶች በአዲስ በማረስ ወደ ምርት እንዲገቡ የተደረገበትና ከባህር ዛፍ ነፃ በማድረግ ወደ ምርታማነት ለመቀየር የተጀመረው ስራ በሁሉም መዋቅሮች በስፋት ሊሰራበት ይገባል።

የሌማት ትሩፋት ስራዎቻችን ከማህበረሰባችን ፋይዳ አንፃር ትልቅ ቦታ የሚይዝ በመሆኑ በጅምር የሚታዩ ስራዎች በሁሉም መዋቅር አስፍቶ መጠቀም ያስፈልጋል ።

በቡናና በቅመማ ቅመም ዘርፍ በተለይ የጉራጌ ቡና እና ሮዝመሪ ብራንድ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ማስፋትና ውጤታማ እንዲሆኑ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።

የህብረት ስራ ማህበራት ውጤታማ እንዲሆኑ በተገቢው መደገፍ ያስፈልጋል በሚል ተነስቷል ።

በዞኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በወቅቱ ለማጠናቀቅ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችን ማሳደግ ይገባል ያሉት አቶ ላጫ በሁሉም የገቢ አርዕስቶች ከኪራይ በፀዳ መልኩ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ አለበት ብለዋል።

ለዚህም የሚሰበሰበው ገቢ ከወጪ በላይ ሆኖ ጤናማ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት፣ ለታክስ ህግ ተገዢ መሆንና የኦዲትና የኢንተለጀንስ ስራችን በተገቢው መጠቀም ያሰፈልጋል ተብሏል ።

ከተሞች በማስዋብ ለነዋሪዎች ምቹና ተመራጭ ከማድረግ ባሻገር በከተሞች አካባቢ በህገወጥነት የተወረሩ መሬቶች ለማስመለስ የተጀመረው ስራ ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የት/ቤቶች ደረጃ ለማሻሻልና መሰረተ ልማት ለማሟላት የተሰሩ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም
በክልል አቀፍ የ8ኛና በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍሎች ፈተና የተመዘገበው የተማሪዎች ውጤት እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ባለድርሻ አካላት በተለይም የትምህርት አመራርና ባለሞያዎች ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ላጫ አስገንዝበዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በግምገማ መድረኩ ላይ እንዳሉት በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እና በመንገድ እንዲሁም በሌሎች የልማት ስራዎች አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

እነዚህ ውጤቶች ለማስመዝገብ የዞኑ አመራር ያሳየው ቁርጠኝነት በማጠናከር ዞኑ ያሉትን እምቅ ሀብቶች በጥራት፣ በጊዜና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ በመፈጸም ህዝቡ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪ አክለውም የዞኑ ህዝብ የመልማት ፍላጎቱ ከፍተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በልማት ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ የላቀ በመሆኑ አቅሙን በማስተባበር ዞኑን የሚመጥኑ ተግባራት ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ አበረታች ስራዎች በማስቀጠል የታዩ ጉድለቶች ከወዲሁ በማረም የቀጣይ የዕቅድ አካል በማድረግ መፈፀም ይኖርባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *