የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች አሸባሪው የህወኃት ቡድን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለማውገዝ በቡታጅራ ከተማ በሰላማዊ ሰልፍ ገለጹ።

ህብረተሰቡ ለጀግናው የሀገር የመከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።በሰላማዊ ሰልፋ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፋት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ያልተዋጠላቸው የውስጥና የውጭ ባንዳዎች ግንባር ፈጥረው ለውጡን ለማደናቀፍ ከመቼው ጊዜ በላይ ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ።በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ላለፋት ዘጠኝ ወራት ሲካሄድ የነበረውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ አርሶ አደሩ ሳይደናገር የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን እንዲሁም የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ህወኃት ቡድን ላይ የያዘውን ያልተገባ አቋም መለስ ብሎ እንዲያጤን ጊዜ ለመስጠት በማሰብ መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፋን የገለጹት አቶ መሀመድ ጀማል ጁንታው ይህንን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በየበረሃው ተበትኖ የነበረውን ሀይሉን በማሰባሰብ እና ለውትድርና እድሜያቸው ያልደረሱ ልጆች በማሰለፍ በአፋርና በአማራ ክልሎች መጠነ ሰፊ ጥቃት መፈጸሙን ተናግረዋል።አሸባሪው የህወኃት ቡድን በአፋር ክልል ግላኮማ በሚባል ቦታ ቀደም ሲል በማይካድራ የፈጸመውን አይነት በንጹኃን ዜጎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙ የጭካኔ ጥጉን የሚያሳይና ታሪክ ይቅር የማይለው መሆኑን አቶ መሀመድ ገልጸዋል።የዞኑ ህብረተሰብ በሀገር ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ችግሩ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከመንግስትና ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን 483 ሰንጋ በሬዎች፣ 6 ሚሊዮን የሚገመት የቁሳቁስ፣ 15 ሚሊዮን የጥሬ ብር በአጠቃላይ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን የገለጹት አቶ መሀመድ ጀማል በቀጣይም የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ነስሩ ጀማል በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በተፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው የጥፋት እጃቸው በሀገራችን በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።የጁንታው ሀገር የማፈራረስ አላማ በጀግናው የመከላከያ ሀይልና በህዝባችን በተባበረ ክንድ መክተን ግብዓተ መሬቱ ለመፈጸም ከመቼው ጊዜ በላይ ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ አቶ ነስሩ ተናግረዋል።የሰልፋ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በሀገራችን ላይ የተቃጣውን የውጭ ጫና በመቃወም እንዲሁም አሸባሪው የህወኃት ቡድን በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት የሚወገዝ ነው ብለዋል።አክለወም ሰልፈኞቹ እንደገለጹት ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን አሸባሪው የህወኃት ቡድን ለመደምሰስ በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት በአካል በመዝመት የሚጠበቅባቸውን በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *