የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች አሸባሪው የህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ የሚያወግዝ እና ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡

ጥቅምት 28/2014
የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች አሸባሪው የህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ የሚያወግዝ እና ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡

የዞኑ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ከሞተ አራት ዓመት የሆነውን ጁንታው የህወሓት ቡድን ግብዓተ ቀብር ለመፈጸም በጋራ መነሳት አለበት ሲሉ ሰለማዊ ሰልፈኞቹ ገለጹ።

በሰላማዊ ሰልፉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሁለት ተቃራኒ ኩነቶች ውስጥ የምትገኝ ማለትም ለዘመናት የተወዘፈውን የህብረተሰቡ የዲምክራሲ እጦት ጥያቄ ምላሽ መስጠት የተጀመረበት በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለመበታተን የውስጥና የውጭ ጠላቶችዋ የህልውና አደጋ የደቀኑበት ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡

አሸባሪዎቹ የህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያልተገባ ጋብቻ ፈጽመዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አቶ መሐመድ ጀማል ይህንን ለመመከት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ እኛ እያለን ሀገር አትፈርስም ይልቁንም ሽብርተኞቹ ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ጠራርገጎ ግብዓተ ቀብራቸውን በመፈጸም የሀገሪቱ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነስቷል ብለዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ማህበረሰብ በሀገሪቱ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ከመንግስትና ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የዞኑ ህዝብ ከ67 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን ድጋፉ በሀገሪቱ የተቃጣው ጥቃት እስኪወገድ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ በመቀልበስ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት እንዲቻል ታላቅ ህዝባዊ ማዕበል በማቀጣጠል የሀገሪቱ ጠላቶች አይቀጡ ቅጣት ቀጥተን ዳግም ስጋት ከማይሆኑበት ደረጃ ለማድረስ አቅም ያለው ወደ ግንባር በመዝመት፣ አቅም የሌለው ገንዘብ በመለገስ፣ስንቅ በማዘጋጀት፣ሞራል በመስጠት፣ ጸሎት በማድረግ እንዱሁም ተደራጅቶ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በመጠበቅ ሁሉም ኃላፊነቱ እንዲወጣ ዋና አስተዳዳሪው አቶ መሀመድ ጀማል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፋ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፋት የጉራጌ ዞን የኢዜማ አስተባባሪና የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸዉ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገሪቱን እያሸበረ ያለው በስልጣን በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ በብሄርና በጎሳ ከፋፍሎ የቀበረው የጥላቻ ቦንብ በማፈንዳት እንዲሁም በጥቅም በገዛቸው ባንዳዎች አማካኝነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የመጣን ጠላት ለመመከት እራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ኩሩ ህዝቦች ያሉባት ሀገር ናት ያሉት አቶ ደምስ ገብሬ አቅሙ የሚፈቅድለት የዞኑ ህዝብ በሙሉ ሀገሪቱ ለመበታተን የተነሳውን ሰይጣን ወደ ሲኦል ለመሸኘት በሚደረገው ጦርነት ግንባር ድረስ በመዝመት ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ሀገር በማዳኑ ስራ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰላማዊ ሰልፋ ሲሳተፋ ያገኘናቸው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣበት ምክንያት አሸባሪዎቹ የህወሓት ቡድንና ኦነግ ሸኔ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሰሩት ያለውን የሀገር ክህደት ተግባራቸውን ለማውገዝና ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ ነው ብለዋል።

አክለውም የዞኑ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን ከሞተ አራት ዓመት የሆነውን ጁንታው የህወሓት ቡድን ግብዓተ ቀብር ለመፈጸም በጋራ መነሳት አለበት ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *