የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ከጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ጋር በመተባበር የጉራጊኛ ቋንቋና ባህል ሊያሳድግ የሚያስችል አፕልኬሽን አስመረቀ።


የጉራጊኛ ቋንቋ በማልማትና በማሳደግ የስራና የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጹ።

ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በምረቃ ፕሮግራሙ ተገኝተው እንዳሉት የጉራጌ ማህበረሰብ የራሱ ባህል፣ማንነት፣ወግ፣እሴት ያለው ሲሆን ያለው ቋንቋ ከማሳደግና ባህሉን በደንብ እንዲተዋወቅ ከማድረግ አንጻር ውስንነቶች የነበሩ ሲሆን ይህንን በቁጭት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የጉራጊኛ ቋንቋ ማሳደግ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ላጫ የአሰራርና የህግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት፣በዞን ምክር ቤት እንዲፀድቅ በማድረግ የስራ ቋንቋ እንዲሆንና የጉራጊኛ ቋንቋ በ1ኛ ክፍል የተጀመሩው የመማር ማስተማር ስራ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ትምህርት እንዲሰጥበት ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆ ስራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል ።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ ዘመን ለመድረስ የጉራጊኛ ቋንቋ ለማሳደግ ጉራጊኛ፣አማሪኛና እንግሊዘኛ መዝገበ ቃላቶች የያዘ አፕልኬሽን ነው ዛሬ በይፋ መመረቁን የገለጹት።

ይህ የበለጸገው የጉራጊኛ አፕልኬሽን ጸሀፊዎች፣ተመራማሪዎች፣አጥኚዎችና ማንኛውም አካል መረጃን በቀላሉ እንዲያገኝ፣ቋንቋው እንዲያድግ እንዲሁም ስለ ጉራጌ ባህልና ቋንቋ ሙሉ እውቀት እንዲኖረው ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።

ጉራጌ ባህሉ፣ቋንቋው ታሪኩ እንዳያድግና እንዳይተዋወቅ የሚፈልጉ ከፋፋይ አካላት እንዳሉ ያስገነዘቡት ወ/ሮ መሰረት በቀጣይ ግን ቋንቋው እንደ ሌሎች ቋንቋዎች እንዲያድግ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት፣ተራዶ ድርጅቶችና ከሙህራን ጋር ተቀናጀተው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው ሲስተሞችን በማልማትና በተቋማት ጥቅም ላይ ማዋል በዚህ ዘመን አማራጭ የሌለው የቴክኖሎጂ ትሩፋት ሲሆን እነዚህም ስራን ያቀላሉ፣ጊዜንና ወጪን ይቆጥባሉ ነው ያሉት።

አቶ ደምስ አክለውም ይህ አፕልኬሽን የጉራጊኛ ቋንቋና ባህል ከመጥፋትና ከብረዛ ለመጠበቅ በሚደረገው ጥረት በቴክኖሎጂ ለማገዝና በትምህርት ቤት የተጀመረው የጉራጊኛ ቋንቋ ተማሪዎች በትርጉም እንዳይቸገሩ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አብራርተዋል።

በመድረኩ የተሳተፉ አካላት እንዳሉት የጉራጊኛ ቋንቋ እንዲያድግና የስራ ቋንቋ እንዲሆን በምክር ቤት ጸድቆ የህግ ማቀፍ እንዲኖረው መደረግ እንዳለበትና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት ይኖርባቸዋል ብለዋል ።

ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸው፣ጉራጊኛ የሚዲያ ቋንቋ መደረጉ እና መሰል አይነት በቴክኖሎጂ ተደግፎ እንዲያድግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዲጠናከሩ ያስታወቁት ሀሳብ ሰጪዎቹ የጉራጊኛ ቋንቋ ተናጋሪው ከራሱ ጀምሮ ጉራጊኛ በማውራት ቋንቋውን ማሳደግ እንዳለበት አስገንዘበዋል።

በመጨረሻም ለስራው ውጤታማነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትና ተቋማት የእውቅና ሽልማት በመስጠት መድረኩ ተጠናቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *