የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት ያሉንን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ተጠብቀው ለትውልድ ለማስተላለፍና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻዎች ለማድረግ ማልማትና ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።
የጉራጌ ማህበረሰብ በባህል፣ በታሪክ ፣በጥበብ፣ በህግ ለዘመናት ያዘለቃቸው በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊ፣ ሃይማኖታዊ እሴት ያሉት ሲሆን እሴቶቹ ይበልጥ እንዲተዋወቁ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ዘመናዊ የፍትህ ስርአት ባልነበረበት ዘመን ፍትህ የሚያሰፍንበት፣ የሚተዳደርበት፣ ጸብ የሚከላከልበትና ጸብ የሚያበርድበት፣ወንጀል የሚያጋልጥበት፣ ተጠያቂነት የሚያሰፍንበት ‹የጆካ ቂጫ› የመሰረተ ማህበረሰብ ነው፣
ከጥንት ጀምሮ ዛሬም ድረስ ያልተሞከረው የገጠር የመኖሪያቤት ፕላን ቀድሞ የጀመረና በተለየ መልኩ ያለምንም የዘመናዊ የምህድስና እውቀት በሃገር በቀል ጥበብ ጀፎረ ቀይሶ ለትውልድ ያሻገረ ማህበረሰብ ነው ብለዋል።
ከማህበረሰቡ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶች መካከል የእናቶችና የልጃገረዶች ቀን ማክበር ተጠቃሽ ሲሆኑ ከአለም አስቀድሞ “አንትሮሽት” የእናቶች የምስጋና ክብር መስጠት ቀን እንዲሁም ” ነቐ” የልጃገረዶች ነጻነት የሚጎናጸፉበት ቀን ቀምሮ ማኖሩ የማህበረሰቡ ብልህነት ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
አያይዘውም የጉራጌ ማህበረሰብ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበትን ጠንካራ የስራ ባህል ሳይደበዝዝ እንዲቀጥል ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።
በዞኑ ያሉት ጸጋዎች ለመጠቀምና ችግሮቹ ለመሻገር ሁሉም የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በዞኑ ያሉ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ጉራጊኛ ቋንቋና የጉራጌ ባህሎች ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ደራሲያንና ባለሙያዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።