የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ በወረዳ ለሚገኙ ህፃናት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

መስከረም 27/2015 ዓ/ም

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ በወረዳ ለሚገኙ ህፃናት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

ከትምህርት ስርዓትና ፖሊሲ አኳያ ትምህርት ለሁሉም ህፃናት መድረስ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት ትምህርት ለሁሉም ሁሉም ለትምህርት በሚል መርሃ ግብር በትምህርት ዘርፉ ላይ በርካታ ተግባራቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ገልፀው ይህን ተግባር ለማስቀጠል ከሁሉም ሴክተር በጀት 1 በመቶ ተቀናሽ በማድረግ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደትምህርት መላክ እንዲችሉ የአካባቢውን ማህበረሰብ፣ የግሉን ባለሀብት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መንግስትን በማስተባበር የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት በርካታ ህፃናት ትምህርታቻን እንዲከታተሉ ማድረግ ተችሏል፡፡

ከዚህ በፊትም ከተቋሙ የስራ ማስኬጃ በጀት ተቀናሽ በማድረግ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስና የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች ለተጋላጭ ህፃናት ድጋፍ መደረጉን የገለፁት ወይዘሮ መሰረት ከተጀመረ ሶስት አመታትን ያስቆጠረው የ1 በመቶ የበጀት ድጎማ የሚመራው በዞን አስተዳደር፣ በፋይናንስና በሴቶችና ህፃናት በተቃቋመ ግብረሀይል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ አወል ጅማቶ የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊና የኮሚቴው አባል እንደገለፁት ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ አንፃር የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ መናር ተከትሎ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደትምህርት ሳይልኩ እንዳይቀሩ ግብረሀይሉ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ችሏል ብለዋል፡፡

አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ልጆች ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል እንዲኖርባቸው መሰል ድጋፎች አጠናክሮ በማስቀጠል ትውልዱን በትምህርት ወደተሸለ ደረጃ ለማድረስ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ነኢማ ቆርቻ የማረቆ ወረዳ፣ ወይዘሮ ለምለም ጉርታ የሙህርና አክሊል ወረዳ ዘቢባ አወል የቀቤና ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡ ቁሳቁሱን ሲረከቡ እንደገለፁት ህፃናት የነገ ሀገር ተረካቢ ተስፋዎች በመሆናቸው እንዲህ አይነት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

እንደሀላፊዎቹ ገለፃ የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ የወቅቱን ችግር ለማለፍ መንግስትና ህዝብ በመደጋገፍ ወቅታዊ ችግሮችን ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት ህፃናት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይፈናቀሉ መንግስትና ረጂ ድርጅቶች ለትምህርት ዘርፉ የሚሰጡትን ትኩረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የተማሪዎቹ ወላጆች በበኩላቸው በአሁን ሰዓት ይህ ድጋፍ መደረጉ እንዳስደሰታቸውና በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ምክንያት ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ በተሰራው ስራ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *