የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበራ ወንድሙ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የፋሲካ በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳቹህ መልዕክት አስተላለፋ!!

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለፋሲካ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፤የፋሲካ በአል በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩና ኢትዮጵያዊ ውበታችንን፣ ባህላችንንና አንድነታችንን ጎላ አድርጎ ከሚያሳዩ በዓሎቻችን ውስጥ አንዱ ነው፡፡

የዘንድሮ የፋሲካ በዓል የምናከብረው ከሌላው ወቅት በተለየ ሁኔታ በርካታ ዜጎች የወገኖቻቸው ድጋፍ በሚሹበትና የኑሮ ውድነቱ የበርካታ ኢትዮጵያውያን እየፈተነ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው። ስለዚህ ይህ የፋሲካ በዓል ስናከብር የገጠመንን የኢኮኖሚ ፈተናና ችግር ባገናዘበና የተቸገሩት ወገኖቻችን እየደገፍን መሆን ይኖርበታል።

የትንሳኤ በዓል የመስዋእትነት ተምሳሌት ነው፣ ሌላውን ለማዳን መሰቃየትን፣ መሰዋዕትነት መሆንን የሚያመለክት ነው። ሌላው የትንሳኤ በዓል ስናስብ ክርስቶስ በህማማቱና በሞቱ እንዲሁም በመከራው የሰው ልጆች ያዳነበትና ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ያሳየበት ነው።

በመሆኑም በዓሉ ህዝበ ክርስትያኑ በእምነቱ አስተምሮት መሰረት ለወገኖቹ ፍፁም ፍቅር የሚያሳይበት፣ይቅር የሚባባልበትና አንዳችን ለሌላችን መሰዋአትነት የምንከፍልበትና የምንደጋገፍበት በአል መሆን ይገባዋል።

ሌላው ክርስቶስ በምድር ላይ ሲመላለስም ሆነ በህማማቱና በሞቱ እንዲሁም በትንሳኤው ሁሉን አድነዋል ነፃ አውጥተዋል፤ የክርስቶስ የትንሳኤው ብርሃን ለሁሉም አጎናፅፈዋል ማንንም አለየም ፤ በመሆኑም እኛም የትንሳኤው በአል ስናከብር ከተለያዩ ከፋፋይና አንድነታችን ከሚሸረሽሩ አጀንዳዎች በመራቅ በፍቅርና አንድነት የተቸገሩትን በመርዳትና በማገዝ መሆን አለበት።

እንደ አቶ አበራ ገለፃ ህዝበ ክርስቲያኑ በፆም ወቅት ሲያደርጋቸው የነበሩ የፀሎት፣ የመተሳሰብ፣ የመረዳዳትና የመደጋገፍ መልካም ተግባራት ቀጣይም ሊያስቀጥላቸው ይገባል።

ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በአል ማክበር የሚቻለው፣ወጥቶ መግባት የሚቻለው፣መፆም መፀለይ የሚቻለው ባጠቃላይ ሁሉም ነገር ማድረግ የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ህዝበ ክርስቲያኑ የፋሲካን በአል ሲያከብር የአካባቢው ሰላም ከፀጥታ አካላት በመተባበር እንደተለመደው ነቅቶ መጠበቅና አንድ አንድ ፀብና ግጭት የሚቀሰቅሱ ግለሰብም ይሁን ቡድን በመከላከልና በማጋለጥ መሆን አለበት።

ምክትል አስተዳዳሪው በመልዕክታቸው ዘንድሮ በዚህ በፆሙ ወቅት ጨምሮ በዞናችን በተለያዩ አካባቢዎች በጥንቃቄ ጉድለት በርካታ የቤት ቃጠሎ አደጋ መድረሱ አስታውሰው በአደጋውም በርካታ ንብረት ወድሟል፣ የህብረተሰቡ ስነልቦና ተጎድቷል ያለመጠለያም ቀርተዋል። በመሆኑም የትንሳኤ በዓል ስናከብር የእሳት አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች ለይቶ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠቁመው እነዚህ በእሳት አደጋ ከቤታቸው ወጪ ያሉ ዜጎቻችን በዓሉ አብረናቸው ልናከብርና የጀመርነው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በመጨረሻም ትንሳኤው የሰላም፣የጤና፣ የአንድነትና የብልፅግና እንዲሆን እመኛለሁ።

በድጋሚ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለትንሳኤው በአል በሰላም አደረሳቹ!!

             መልካም_በዓል!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *