የጉራጌ ዞን መስተዳድር ምክር ቤት የ2016 በጀት አመት የመንግስት ስራዎች አፈጻጸም ግምገማ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በግምገማው ወቅት እንዳሉት በበጀት አመቱ ሁሉንም አቅሞችን በመጠቀም የዞኑ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

የመንግስት ወጪ ቅነሳ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት እንደሚገባ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ዞኑ የሚያመነጨውን ሀብት አሟጦ በመሰብሰብ የውስጥ የገቢ አቅም ለማሳደግ ሁሉም አመራር ለዘርፉ የተለየ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።

በግብርና ልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ መቻሉንና በዘርፉም ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም በባህር ዛፍ የተሸፈኑ መሬቶችን እንዲታረሱ በማድረግ በፍራፍሬና በቋሚ ሰብሎችን ለመተካት የተጀመሩ ስራዎችን በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዞኑ ህብረተሰቡና መንግስት በመቀናጀት የትምህርት ስብራት ለመጠገን የሚያስችሉ የትምህርት መሰረተ ልማቶች ግንባታና ግብዓት ከማሟላት በተጨማሪ በመንገድ ልማት ዘርፍም ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በዞኑ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የሰላምና የጸጥታ ስራዎችን አስቀድሞ መከላከልን መሠረት አድርጎ በመስራት የህግ የበላይነት ማረጋገጥ፣ የከተማ ውበትና ጽዳት ስራ፣ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ማጠናከር፣ የተጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶች ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት በዞኑ በሁሉም መስኮች የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።

በትምህርት፣ በግብርና፣ የኑሮ ውድነት ለመቀነስ የሰንበት ገበያዎችን በማቋቋም አምራችና ሸማች በቀጥታ የማገናኘት ስራ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመንገድና በሌሎችም ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በዞኑ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም በተለይ የወልቂጤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *