የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ከመማር ማስተመሩ ጎን ለጎን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ወረዳዎችን በማስተባበርና ከተቋሙ ካለው ውስን ሀብት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት 2 መቶ ሺ ብር ድጋፍ እንዲሁም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ለሁለተኛ ዙር የ30ሺ ብር የቦንድ ግዢ በዛሬው እለት በመፈጸም ለዞኑ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ርክብክብ ፈጽሟል።

መምህራን ማህበሩ የ2014 ዓ.ም 1ኛ ሩብ አመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ የወረዳ እና ከተማ መስተዳደር መምህራን ማህበር ሰብሳቢዎችና ሌሎች ባለድር አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ አመርጋ በርክብክቡ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ከመምህራን ማስተማር ጎን ለጎን በየጊዜው ለህዳሴው ግድብና ለመከላከያ ሰራዊት ደጋፍ ማድረጋቸው ከፍተኛ የሆነ የሀገር ፍቅር እንዳለቸው አመላካች ነው ብለዋል።

መምህራን አንድ ከሆኑ ሀገር ማንቀሳቀስ እና በሀገር እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት ይችላሉ ያሉት አቶ አበበ የሚያከናውኑዋቸው ተግባራት በጥቃቅን ጉዳዮች ሳይደናቀፉ መሰራት እንዳለባቸው አሳስበው ላደረጉት ድጋፍም በዞኑ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ንዳ በበኩላቸው መምህራን ማህበሩ ከመንግስት ጎን በመሆን የትምህርት ጥራቱ እንዲጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ያሉ ሲሆን ልክ በኮሮና ጊዜ እየከፈለው የነበረ መስዋዕትነት በቀጣይም አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ እንደገለፁት የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ለመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ለህዳሴው ግድብ እና በሌሎችም ተግባራት በሚያደርገው ተግባር ለክልሉ ባሉ መምህራን ማህበራትም ግንባር ቀደም ነው ብለዋል ።

አሁን የኮሮና ቫይረስ እየተዛመተ በመሆኑ መምህራንና ተማሪዎች እርቀት በመጠበቅ፣ ማስክ በማድረግና ሌሎችም የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማህበሩ ተጠናክሮ መስራት እናዳለበት ያሳወቁት አቶ አማኑኤል የወባ በሽታ እንዳይዛመት ትምህርት ቤቶች አካባቢ የተጠራቀሙ ቆሻሻዎችን በማስወገድ ተማሪዎች ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራበት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ በርታ ያረቢ ማህበሩ ከ10ሺ በላይ አባል ያለው ሲሆን የመምህራን ጥቅማ ጥቅም የማስጠበቅ ፣ ለማህበሩ በጀት እንዲያዝ ከማድረግ ፣የትምህርት ደረጃ ከማሻሻል፣ የደረጃ እድገት ከመስጠት እና በሌሎች ዘርፎችም በርካታ ስራዎች እየሰራ ያለ ማህበር እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በሀገራዊና ዞናዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ስራዎች የሚሰራ ማህበር መሆኑን ያሳወቁት አቶ በርታ ለመከላከያ ሰራዊት 2መቶ ሺ ብር እና ለህዳሴው ግድብ ደግሞ 30 ሺ ብር ድጋፍ መደረጉ እና ድጋፋም እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

ለቀጣይም ማህበሩ ለማጠናከር እና የራሱ ገቢ እንዲኖረው ታሳቢ በማድረግ ሜጋ ፕሮጀክቶች ለመስራት ከዞኑ አሰተዳደር እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የመምህራን ጥቅማ ጥቅም በሚፈለገው ልክ ያለማስጠቀም እንዲሁም የክፍያ መዘግየት እና ሌሎችም ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ ተነስቷል።

መምህር አቦነህ ከበደ እና መምህርት ራህመት ኪዳኔ የወረዳ የመምህራን ማህበር ሰብሳቢ ሲሆኑ የወረዳቸው መምህራኖች ከማስተማር ጎን ለጎን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ አጋርነታቸውን እያሳዩ እንደሆነ ተናግረዋል።

አክለውም ከመምህራን የሚመጡ ቅሬታዎች ካሉ ወደ ሚመለከተው አካል ድረስ ተደራሽ በማድረግ መፍትሄ እንዲያገኙ በትኩረት እየሰሩ እንደሆነ ያስታወቁት ሰብሳቢዎቹ በቀጣይም የማህበሩ አላማ ለማሳካትና ውጤታማ ስራ ለመስራት በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል ሲል የዘገበውየጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *