የጉራጌ ብሔረሰብ የነቖ( የልጃገረዶች በዓል) በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ቆጠር ገድራ ቀበሌ ነቖ (የጉራጌ ልጃገረዶች ቀን ) በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

የጉራጌ ብሔረሰብ በርካታ ባህላዊና ትውፊታዊ ባህሎች ባለቤት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ኧረቖ/ነቖ (የልጃገረዶች ቀን) አንዱ ነው።

ነቖ(የልጃገረዶች ቀን) በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ በጥር ወር ላይ ወይም ገና በዋለ በ15ኛው ቀን ባሉት ጊዜያት በሴት ልጃገረዶች የሚዘወተር ባህላዊ ጨዋታ እንደሆነ ይታወቃል።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በዓሉ ተገኝተው እንዳሉት ነቖ(የልጃገረዶች) በዓል ጥር ወር ላይ ተገናኝተው ተሰብስበው የሚበሉበትና የሚጠጡበት፣ እቅድ የሚያወጡበትና የሚወያዩበት፣ የሚተጫጩበት ብሎም ነጻነታቸው የሚያውጁበት በዓል ነው።

የነቖ በዓል ለማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ ልጃገረዶች በዓሉ በሚያከብሩበት ወቅት ከጓደኞቿቸው ጋር በግልጽ ሀሳባቸው የሚገልጹበት፣ ለአቅመ ሄዋን ከደረሱ ለጓደኛቸው አማክረው የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑበት እንዲሁም በራስ የመተማመን ብቃታቸውን ከማሳደግ ባለፈ በስነልቦና ጭምር ጠንካራ ሆነው ውበታቸውና ማንነታቸውን አደባባይ ወጥተው በመግለጽ የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አንጻር የነቖ በዓል በበለጠ በመስራት የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ለማህበረሰቡ በተለያየ መልኩ እንዲጠቀም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ብሔረሰብ ቀድሞም ለሴት ያለው መልካም አመለካከት፣ ቀድሞ ዴሞክራሲ የተለማመደ እንዲሁም በሴት ልጅ ነጻነት የሚያምን ማህበረሰብ መሆኑን ነቖ፣ አንትሮሸት አመላካች ናቸው ያሉት ወይዘሮ መሰረት መሰል ባህሎች ከመቀዛቀዝ በመውጣት በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም መዳረሻ ጭምር እንዲሆኑ መምሪያው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው እነዚህም ተጥብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።

የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ በበኩላቸው በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ነቖ ከባህላዊ ይዘቱ ባሻገር ሴት ልጃገረዶች ነጻነታቸው በማወጅ ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክሩበት የነጻነት በዓል ነው ብለዋል።

ይህ በዓል በቀጣይ በተሻለ መልኩ እንዲከበርና ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ያሉት አቶ ዘውዱ የወረዳው መንግስትም በዓሉ እንዲጠናከር ብሎም ዘርፉ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም አመላክተዋል።

የእዣ ወረዳ ባህል ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ የሽነሽ ተካ እንዳሉት ኧረቖ/ ነቖ ሴት ልጃገረዶች ነጻነታቸውን የሚያውጁበትና ደስታቸዉን የሚገልጹበት በዓል ነው።

በዓሉም በጥር ወር የሚከበር እንደመሆኑ መጠን ከታህሳስ ወር ጀምሮ ለበዓሉ የሚሆን ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግ ያነሱት ኃላፊዋ ለዚህም ሴት ልጃገረዶች ቤት ለቤት እየዞሩ ብር፣ በአይነት ገብስና አተር የሚሰጣቸው ሲሆን ታላላቆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ለበዓሉ የሚሆኑ አይብ፣ ክትፎ፣ ቆሎ፣ በሶ እና ሌሎችም አዘጋጅተውላቸው እንደሚያከብሩም አውስተዋል።

ይህ ባህላዊ የልጃገረዶች በዓል ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንዳለበትም አመላክተዋል።

በበዓሉ የተሳታፉ ሴት ልጃገረዶች እንደገለጹት በዓሉ ከተቀዛቀዘበት በመውጣት በደመቀ መልኩ በመከበሩ ደስታቸው ወደር ዬለሽ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህ የሴት ልጃገረዶች በዓል ቀን በጥር ወር የሚከበርና ማህበራዊ መስተጋብሮቻቸውን የሚገልጹበት ሲሆን ለበዓሉም በርካታ ዝግጅቶች በማድረግ በድምቀት እንደሚከበርም አስረድተዋል።

በዓሉ አሁን ላይ ከመቀዛቀዝ ወጥቶ እንዲያንሰራራ የሚደረገው ጥረት አመስግነው በቀጣይ በዓሉ በበለጠ እንዲከበር ብሎም እንዲተዋወቅ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

በበዓሉም የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ፣ የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ፣ የእዣ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ ሙከረም በደዊ እና የወረዳው የስራ ኃላፊዎች፣ የቆጠር ገድራ ቀበሌ ነዋሪዎችና ሌሎም ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *