የጉራጌ ብሔረሰብ አንድነትን የሚያጠናክሩ ልማቶች በማፋጠን ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ማህበሩ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

የጉራጌ ብሔረሰብ አንድነትን የሚያጠናክሩ ልማቶች በማፋጠን ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ማህበሩ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ባካሄደው አመታዊ ጉባኤው የተለያዩ የቀጣይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ተጠናቋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ እንዳሻው ጣሰው በጉባኤው ማጠቃለያ በሰጡት የቀጣይ አቅጣጫ እንዳሉት ማህበሩ የጉራጌ ብሔረሰብ አንድነትን የሚያጠናክሩ ልማቶች በማፋጠን ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል።

የጉራጌ ብሔረሰብ ባህላዊ እሴቶች፣ ቋንቋና ታሪክ በማልማት ሳይደበዝዝ ተጠብቆ ለተተኪው ትውልድ የማስተላለፍ ስራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

ማህበሩ ህልውናውን አስጠብቆ የተለያዩ ልማቶች በፍትሃዊነት እንዲሰራ የገቢ አቅሙ ማሳደግ እና ቴክኖሎጂ በመጠቀም አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት የጉራጌ ብሔረሰብ በሁለት አስተዳደር የሚመራ አንድ ህዝብ ነው።

ባለሀብቶች ለልማት ሁልጊዜ ገንዘብ ስጡ ከማለት ይልቅ ባለው የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ አካባቢያቸው ገብተው እንዲያለሙ አቶ ላጫ ጥሪ አቅርበዋል።

በቀጣይ ማህበሩ የጀመራቸው የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የጉራጌ ተወላጆችና የልማት አጋሮች በማስተባበር ርብርብ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።

የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በበኩላቸው የልማትና የባህል ማህበሩ ተቋማዊ አቅሙ በማሳደግ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች እንዲሰራ የተጀመረውን ሪፎርም የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ጉራጌ በሁለት የዞን አስተዳደር እንዲደራጅ ሲደረግ ማህበረሰቡ በልማትና በባህል አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡ አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሆነ አቶ ሙስጠፋ ገልጸዋል።

ጉልባማ ከዚህ ቀደም በልማት ላይ በሰራው ልክ በባህል ያልሰራ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የገለፁት አቶ ሙስጠፋ ተወላጅ ባለሀብቶችም ወደ አካባቢያቸው ገብተው እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል።

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቅባቱ ተሰማ ለጉባኤው ሪፓርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ማህበሩ ከረጂ ድርጀቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍና በህብረተሰብ ተሳትፎ በሁለቱም ዞኖች በደቡብ ሶዶና በጉመር ወረዳዎች ት/ቤት፣ የጤና ኬላ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታዎች በማካሄድ ማህበረሰቡ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

የማህበሩ የቡታጅራ ሁለገብ ህንጻ ጂ+1 ወለልን በማጠናቀቅ ማከራየት የተቻለ ሲሆን የአዲስ አበባ የባህል ማዕከል ህንጻ አንደኛው ክንፍ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

የጉራጌ ብሄረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ሰነዶችን በጽሑፍ መሰነድ፣ የጉራጊኛ ቋንቋ የትምህርትና የስራ ቋንቋ እንዲሆን የፊደል ገበታና ቃላት ማደራጀት እንዲሁም የጉራጊኛ ቋንቋ በአንደኛ ክፍል ደረጃ እንዲጀመር ከዞኑ አስተዳደርና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመስራት የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አቶ ቅባቱ ተሰማ ተናግረዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሁሉም የጉራጌ ተወላጆች የማህበሩ አባል በማድረግ የውስጥ ገቢ አቅም ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የጉራጌ ተወላጅ ምሁራኖች የማህበረሰቡ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶች በማጥናት ባለሀብቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ የሚሆኑበት የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ወደ ተግባር በመቀየር ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *