በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ታላቅ የጎዳና ሩጫ ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በሀገሪቱ ታሪክ ግጭቶች ሌላ ግጭት እየወለዱ የግጭት አዙሪት ውስጥ ተነክረን ሰላም አልባ ዘመናትን አሳልፈናል።
ለዚህም በሀገር ደረጃ ባለፉት ዓመታት ሰላም ለማስፈን ማህበረሰቡ ያሳተፈ የዳበረ ዴሞክራሲን የማጽናት፣ የላቀ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር፣ ማህበራዊ ሀብቶችና ባህላዊ እሴቶችን ለመገንባት በርካታ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
የጉራጌ ብሔረሰብ ሰለ ሰላም ጠቀሜታ አስቀድሞ በመረዳቱ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ተባብሮና ተከባብሮ በፍቅር እንደሚኖር የገለጹት አቶ ላጫ ጋሩማ
በዞኑ የተጀመረው ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎችን እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በዞኑ በወልቂጤ ከተማ፣ በእኖር ኤነር መገር ወረዳ ቆሴ ዙሪያ እንዲሁም በአበሽጌ ወረዳ ያሉ የፀጥታ ችግሮች እልባት ለመስጠት የሚያስችል ስራዎች በየደረጃው እየተሰሩ መሆናቸውን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
የዞኑ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን የአካባቢውን ሰላም ዘብ በመቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ አቶ ላጫ ጥሪ አቅርበዋል።
የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው በበኩላቸው የከተማው ነዋሪዎች በሰላም ወዳድነታቸው ቀድሞውኑ የሚታወቁ በመሆናቸው በተደጋጋሚ ስለ ሰላም እያስመሰከሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ሀገሪቱ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ሰላም ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው በከተማው የተጀመረው ዘላቂ የሰላም እሴቶችን ማጎልበት ይገባል።
በከተማው የሚከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
አንዳንድ የሩጫው ተሳታፊዎች እንዳሉት በየጊዜው የሚደረጉ የሰላም ሩጫዎችን የህብረተሰቡን አንድነት፣ አብሮነትና ሰላም ለማጠናከር ሚናቸው ትልቅ ነው።
በዞኑም ሆነ በከተማው ያለውን ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲሚወጡ ገልጸዋል።
በውድድሩም ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያ፣ የገንዘብና የሰርተፍኬት ማበረታቻ ተበርክቶላቸዋል።