የጉራጌ ብሄር ባህላዊ ዕሴት በመጠበቅና በልማት በማስተሳሰር አንድነቱን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር አስታወቀ።

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ የብሔሩ ተወላጆች በተገኙበት በቡታጅራ ከተማ በድምቀት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የጉልባማ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ጀማል ጉባኤው በንግግር ሲከፍቱ እንደገለጹት የልማት ማህበሩ በሁለት ቦርዶች ይመሩ የነበሩ አደረጃጀቶች በማዋሃድ የልማትና የባህል ማህበር በማደራጀት ጠንካራ አንድነት ለዘላቂ ልማት ቴሌቶን አካሂዶ ሀብት በማሰባሰብ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ስራዎችን አከናውኗል ።

ሆኖም ማህበሩ በነበረው ጥንካሬ እንዳይቀጥል በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የተፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነት ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የጉራጌ ተወላጆች የማህበሩ አባል አድርጎ ገቢ በማሰባሰብ የልማት ስራ ለመስራት ምቹ ያልነበረ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ጀማል ገለጻ የልማት ማህበሩ በሀገሪቱ ለውጡን ተከትሎ በተፈጠሩ ችግሮች ውስጥም ሆኖ የጉራጌ ብሔር ዕርስ በርሱና ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለው ትስስር የበለጠ ጠንካራና ዘላቂ መሰረት ላይ የቆመ እንዲሆን አድርጓል።

በዚህም ህብረተሰቡ በማሳተፍ በየወረዳዎቹ በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ የልማት ክፍተቶች በመለየት በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመንገድ፣ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎች የልማት ስራዎች ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማትና የባህል ስራዎች ማከናወን መቻሉን አቶ መሀመድ ጀማል ተናግረዋል።

አክለውም ማህበረሰቡ በማሳተፍ፣ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋትና ብቁ የሰው ኃይል በመፍጠር የማህበሩ የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በየደረጃው ሊካሄድ ይገባል ብለዋል።

የጉልባማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቅባቱ ተሰማ ሪፓርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት ከተለያዩ ረጂ ድርጅቶች ጋር ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ ውል በመግባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የትምህርት ቤት ግንባታ እና የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት፣ በጤና ተቋማት የብሎክ ግንባታና የመታከሚያ አልጋ አቅርቦት አንዲሁም የተለያዩ የልማትና የባህል ስራዎችን ማህበሩ አከናውኗል ብለዋል ።

አያይዘውም አቶ ቅባቱ በሪፓርቱ እንደጠቆሙት የገጠር ገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋማት የአቅም ግንባታ ስልጠና የመስጠትና የቢሮ መገልገያ ቁሳቁስ ማሟላታቸውን ተናግረዋል።

አክለውም የጉልባማ ስራ አስኪያጅ ሪፓርት ሲያቀርቡ እንዳብራሩት በቡታጅራ ከተማ በመገንባት ላይ የሚገኘው የጉልባማ ዋና ጽ/ቤት የመጀመሪያ ወለል ግንባታ አልቆ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ለባንኮችና ለንግድ ተቋማት ማከራየት የተቻለ ሲሆን ቀሪው የግንባታ ስራ በመካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታና የጉልባማ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በበኩላቸው ጉራጌ በራስ አገዝ የልማት ድርጅት ተደራጅቶ አካባቢውን ማልማት ከጀመረ ረጅም አመታት ቢሆን በሂደት መቀዛቀዝ በመታየቱ በ2002 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ቴሌቶን በማካሄድ እንደገና የማጠናከር ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት ለልማት ትኩረት በማይሰጠበት ወቅት መንገድና በመሳሰሉ ስራዎች ትኩረት አድርጎ ሲሰራ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ጊዜ እነዚህ የልማት ስራዎች በመንግስት በትኩረት እየተሰሩ በመሆናቸው ጉልባማ የህብረተሰቡን አንድነት በሚያጠናክሩ ስራዎች በተለይም በባህል፣ በቋንቋና ስፓርት በሌሎችም ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አቶ ሺሰማ ተናግረዋል።

የጉልባማ ኦዲት ኢንስፔክሽን ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ንጉሴ አስረስ ሪፓርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ማህበሩ አቅዶ የሚሰራቸው ስራዎችን ክትትል በማድረግ ኦዲት የማድረግ ስራ መሰራቱን ተናግረው በተለያዩ ሀገራዊና ወቅታዊ ችግሮች ምክንያት በአጠቃቃላይ አፈጻጸም ጉድለቶች መኖሩን ተናግረዋል።

በቀጣይ የዞኑ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር እና የማህበሩ አባላቶች በማብዛት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንዲጠናቀቁ ርብርብ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች በስጡት አስተያየት የማህበረሰቡ ውስጣዊ አቅም አቀናጅቶ ለልማት ከማዋል አንጻር ጉድለት መኖሩን ገልጸው በቀጣይ ህብረተሰቡ ለልማት የሚያነሳሳ ንቅናቄ መካሄድ አለበት ብለዋል።

በጉባኤው የጉልባማ አመታዊ የስራ አፈጻጸም፣ የውስጥና የውጪ የኦዲት ሪፓርት፣ የቀጣይ ስራ ዕቅድና የንቅናቄ መፍጠሪያ ሰነድ ቀርበው ዉይይት ተደርጎባቸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:-
https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *